
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ሚኒስቴር መሪዎች፣ የሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ እና የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች እና የቱሪዝም ባለሙያዎች በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ ነው።
በጎንደር ከተማ ተገኝተው የታሪካዊ ቅርሶችን ጥገና እና የኮሪደር ልማቶችን መመልከታቸው የሚታወስ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ እያደረጉት ባሉት ምልከታም በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
እንግዶቹን ተቀብለው ሥለ ተቋሙ ሥራዎች ገለጻ ያደረጉት የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ በጥቂት ተጀምሮ አሁን ላይ ግን ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ጭምር በመጠቀም የሚሠራ ተወዳዳሪ የመገናኛ ብዙኀን ተቋም ነው ብለዋል። አሚኮ ሁኔታዎች ሳይገድቡት በጽናት በመቆም ለሕዝብ የሚሠራ ተቋም ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የክልሉ የቱሪዝም ሃብቶች እንዲተዋወቁ እና መልካም እሴቶች እና ወጎች እንዲጎለብቱ ተገቢውን የመገናኛ ብዙኅን አገልግሎት እየተሠጠ ስለመኾኑም ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ተናግረዋል። አሚኮ ዘመናዊ የመገናኛ ብዙኅን መሣሪያዎችን የታጠቀ፣ ቀድሞ የሚደርስ እና የሕዝብ ባሕል እና እሴቶችን ለዓለም የሚገልጥ ተቋም ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ተቋሙ ሃይማኖታዊ በዓላትን ጭምር ሽፋን የሚሰጥ፣ የቱሪዝም ዘርፉም ትርጉም ባለው መልኩ እንዲያድግ እየተጋ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
አሚኮ ከክልሉ ሕዝብም አልፎ ለመላ ኢትዮጵያውያን ተደራሽ የኾነ ሚዲያ ነው ያሉት ጋዜጠኛ ሙሉቀን ይህንን ተደራሽነቱን የበለጠ ለማስፋትም አዲስ አበባ ላይ ዘመናዊ ሥቱዲዮ መገንባቱን አንስተዋል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችም ስቱዲዮዎች ተገንብተው የተሟላ አገልግሎት እየተሠጠ መኾኑን ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አብራርተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ አሚኮ ለሀገር እድገት የሚበጅ የመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ጠንካራ ተቋም ስለመኾኑ ተናግረዋል። “ሚዲያ ለቱሪዝም እድገት ዋነኛ መሣሪያ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሚኮም በሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞቹ የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ተቋሙ የክልሉን የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታዎች፣ ብርቅዬ እንስሳት፣ ባሕል፣ እሴት እና ሌሎችንም የቱሪዝም ሃብቶች ለማስተዋወቅ ግንባር ቀደም ስለመኾኑ ጠቅሰው “አሚኮ የቱሪዝም አምባሳደር ሚዲያ ነው” ሲሉም ገልጸውታል።
አሚኮ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በሚከበሩበት ቦታ ሁሉ በመገኘት ጠንካራ የኾነ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን የሚሰጥ ሚዲያ ነው፣ ከዚህ ጥንካሬውም ሌሎች መገናኛ ብዙኅን ልምድ ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ፀጋዬ አሚኮ ጊዜውን የዋጁ ድንቅ ቴክኖሎጅዎችን ይዞ የሚሠራ ተቋም መኾኑን በአካል ተገኝተው ማየታቸውን ተናግረዋ። አሚኮ እርሳቸው ለሚያሥተዳድሩት ገዳምም በቅርበት የሚያገለግል መገናኛ ብዙኀን ስለመኾኑ ገልጸዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በቅዱስ ላሊበላ በልዩ መልኩ የሚከበር ነው፣ አሚኮም በችግር ወቅት ሳይቀር በየዓመቱ እየተገኘ ይህንን ድንቅ በዓል ለዓለም እያሳየ እና እያስተዋወቀ ያለ አገልጋይ ተቋም ነው ብለዋል አባ ሕርያቆስ።
“አሚኮ ላሊበላን ብቻ ሳይኾን በዙሪያው የሚገኙ ቅርሶችንም ጭምር በትጋት በማስተዋወቅ እንደቤተሰብ ቀርቦ እያገለገለን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
መጭው የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልም እየቀረበ መኾኑን እንግዶችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል። አሚኮም እንደተለመደው በቦታው ተገኝቶ በዓሉን እና አጠቃላይ ሥርዓቱን ለዓለም እንዲያሳይ ጋብዘዋል።
የላስታ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ላስታወርቅ አያሌው አሚኮ እያደገ የመጣ፣ ዘመናዊነትን የታጠቀ እና እውነትም ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ ተቋም ነው ብለዋል።
በርካታ ቅርሶች በሚገኙበት ክልል የበቀለ ተቋም ነው፤ እነዚህን ሃብቶች ለማስተዋወቅም የሚተጋ ነው፤ በላስታ ወረዳ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስተዋወቅም ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።
ከላሊበላ ከተማ አስጎብኝዎች ማኅበር የመጡት ሻምበል ካሳ በበኩላቸው “አሚኮ በዚህ ልክ የተደራጀ ትልቅ ሚዲያ መኾኑን አይቸ ተደንቄያለሁ” ብለዋል።
አሚኮ በበርካታ ቋንቋዎች የሚያገለግል የክልሉ ሁነኛ ሀብት መኾኑንም ተናግረዋል። የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ሃብት እንዲፈጠርም የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
