ኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ጤናማ ትውልድ መገባት ያስፈልጋል።

8
ገንዳ ውኃ: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በዓለም ለ38ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው። በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውኃ ከተማም ተከብሯል።
የኤች አይ ቪ ኤድስን ቀን ሲያከብሩ ያገኘናቸው አቶ ሻበል ሰሎሞን የፋና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለባቸው እና ለ23 ዓመታት አብሯቸው እንዳለ ተናግረዋል። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያወቁት ከ23 ዓመት በፊት በመከላከያ ሚንስቴር ተመልምለው ወደ ውጭ ሀገራት ለመሄድ ምርመራ ባደረጉበት ጊዜ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስተው የኤች አይቪ መድኃኒት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ስለቫይረሱ አስከፊነት ለማኅበረሰቡ እየተዘዋወሩ ሲያስተምሩ እንደነበር ነግረውናል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ የኾኑት እና በጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤቱ በጎ አድራጎት የኤች አይ ቪ ኤድስ አቻ ለአቻ ውይይት መሪ ወይዘሮ የሺሀረግ ወርቁ ሴተኛ አዳሪዎች ራሳቸውን ከበሽታ እንዲከላከሉ የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ስለኤች አይ ቪ ኤድስ ብቻ ሳይኾን ስለሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ጭምር ከመከላከል እስከ ሕክምና ድረስ ትምህርት እንደሚሰጡ ነው ያስረዱት። በቫይረሱ የተያዙ አካላትንም ከማኅበረሰቡ እንዳይገለሉ ሰፊ ሥራዎችን እንሠራለን ነው ያሉት።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የኤች አይ ቪ ኤድስ አስተባባሪ ኦፊሰር ታሪኩ አስፋው ኤች አች አይ ቪን ለመከላከል ከዚህ ቀደም ሰፊ ሥራዎች እንደተሠሩ ተናግረዋል። አሁን ላይ ግን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንዳልኾነ እና የመዘናጋት አዝማሚያዎች ይታያሉ ብለዋል።
ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ለሴተኛ አዳሪዎች፣ ለረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች እና በትምህርት ቤት ለተማሪዎች ትምህርት ይሰጣል ነው ያሉት።
ባለፈው በጀት ዓመት የኤች አይ ቪ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ውስጥ ከ270 በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው አስረድተዋል።
ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን ሰዎች ማኅበር መስርቶ በማደራጀት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ታሪኩ ገልጸው ስለበሽታው ለማኅበረሰቡ ትምህርት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
ኤች አይ ቪን በመከላከል ጤናማ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ አስተባባሪው ተናግረዋል። እንደዞን ለበሽታው ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበባሕር ዳር ዲስትሪክት ሥር የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መስጠት ጀመሩ።
Next articleበሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርም ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል።