በባሕር ዳር ዲስትሪክት ሥር የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መስጠት ጀመሩ።

3
ባሕርዳር፡ ኅዳር 22/2018ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሱፐርቫይዘር ሀሌሉያ ዘላለም ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለማውጣት አካታች የኾኑ ወደ 33 የሚጠጉ የመታወቂያ አይነቶች ሲስተም ላይ መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የባንክ ደብተር ነው ብለዋል። ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዝርዝር መረጃ ስለሚሰጥም በአገልግሎት ሰጭው ባንክ እና በተገልጋይ ማኅበረሰቡ ላይ መተማመን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መታወቂያዎች መኖራቸውን የገለጹት ሱፐር ቫይዘሩ እነዛ መታወቂያዎች የሚያረጋግጡት ውስን የኾነን ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል።
በልዩ ሁኔታ ሙሉ መረጃ ስለሚሰጥ ማንነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለመጭበርበር የተጋለጠ አለመኾኑንም አንስተዋል። ማኅበረሰቡ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን ይዞ ለአገልግሎት በሚሄድባቸው ተቋሞችም ብቁነትን ወይም ደግሞ ነዋሪነትን የሚያረጋግጡ ሌሎች መታወቂያዎችን (የቀበሌ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርት…) ሊጠየቅ እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በሚያስፈልግበት ጊዜ ግን ካርዱን መያዝ ሳይጠበቅ 12 አሐዝ ያለውን የመታወቂያው ቁጥር በመያዝ ብቻ ተገልጋዮች አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሕር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር ደሞዜ ባልቢ በባሕር ዳር ዲስትሪክት ስር በሚገኙ 78 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በአማራ ክልል በሚገኙ በሁሉም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በአሻራ የተደገፈ የግለሰቦችን ትክክለኛነት የሚገልጽ ሁሉን አቀፍ መረጃ የሚይዝ በመኾኑም ባንኩን እና ግለሰቦችን ከመጭበርበር ይታደጋል ብለዋል።
እንደ ሀገር የተያዘ ፕሮጀክት ከመኾኑ ጋር ተያይዞም በቀጣይ ይህን መታወቂያ ላልያዘ ተገልጋይ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚኾን አንስተዋል።
ያ ከመኾኑ በፊት ማንኛውም ኅብረተሰብ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን እንዲጠቀም ነው ያስገነዘቡት። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የገጠሩን ማኅበረሰብ ጨምሮ ሁሉም ሰው ተጠቃሚ መኾን እንዲችል ይሠራል ብለዋል።
ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሕር ዳር ዲስትሪክት አሻራ እየሰጡ ያገኘናቸው ፀጋው ጫኔ ደግሞ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ከቀበሌ መታወቂያ ተሻሽሎ የሚሠራ በመኾኑ ልዩ እና ዘመናዊ ነው ብሏል።
በባሕር ዳር ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤዛዊት ቅርንጫፍ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ለማውጣት መረጃ ስትሞላ ያገኘናት ሃይማኖት ጋሻውም ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያዊነትን ለማረጋግጥ እንደሚያስፈልግ ነው የነገረችን።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአፍላ ወጣት እና ወጣት ሴቶች የኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጮች በመኾናቸው በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ጤናማ ትውልድ መገባት ያስፈልጋል።