የጤና አገልግሎት ግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ውጤት ሊያመጡ በሚችል መልኩ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ፡፡

191

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአማራ ክልል ጤና ቢሮን የኮሮናቫይረስ መከላከል እና መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሥራዎች ገምግሟል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ታሪኩ በላቸው በቢሮው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እና ተፅዕኖን ለመቀነስ ስድስት የተለያዩ ቡድኖች ተቋቁመው እየሠሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በወረርሽኝ ቅኝት ክትትል እና ምላሽ፣ በግብዓት አቅርቦት እና ፋይናንስ፣ በተግባቦት እና ኅብረተሰብ ተሳትፎ፣ በዕቅድ ዝግጅት እና መረጃ ጥንቅር እንዲሁም በሥነ ጽዳት እና ሥነ ንጽሕና ቡድኖች የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የተሠሩ ሥራዎች እና ውስንነቶች ናቸው በዝርዝር የቀረቡት፡፡

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በተለይም ክልሉን በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች የቤት ለቤት ቅኝት እና ግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች አፈፃፀም በዝርዝር ታይቷል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች የተሠሩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ፈታኝ እንደነበሩም ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል፡፡ በክልሉ 45 የለይቶ ማቆያና የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት ዝግጅት መደረጉም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አካባቢ ማዕከላቱ ውስንነት የነበረባቸው እና በበቂ ያልተዘጋጁም እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡ በክልሉ ያሉ አብዛኞቹ የለይቶ ሕክምና ማዕከላት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደነበሩ ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አለመኖርና ያለው የለይቶ ማቆያ ከውጪ ከሚገባው የሰው ብዛት ጋር አለመጣጣሙ ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደበረም ጠቅሰዋል፡፡

ቫይረሱ በክልሉ መከሰቱ በታወቀባቸው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሙሉ ኃይሉን የኮሮናቫይረስን መከላከል ላይ በማድረጉ በመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ላይ ክፍተቶች ተፈጥረው እንደነበርም ምክትል ኃላፊው አንስተዋል፡፡ በጤና መሠረተ ልማት ግንባታ መጓተት እና በግብዓት አቅርቦቶች ላይ የነበሩ ውስንነቶችም ለቋሚ ኮሚቴው ቀርበዋል፡፡

የክልሉን ጤና ቢሮ ዝርዝር አፈፃፀም ሪፖርት የሰሙት የምክር ቤቱ የሰው ሀብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፋንቱ ተስፋዬ በተለይም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ ውስንነቶች እንዳሉበት የጠቀሱት ወይዘሮ ፋንቱ ውጤቱ በየጊዜው እየተገመገመ መመራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የምርመራ ማዕከላት ማስፋፊያ እና የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የክልሉ አቅም በሚፈቅደው ልክ እንዲጠናከር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የግብዓት ስርጭት ፍትሐዊነት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እየተለዩ ሊሠሩ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡
በመሠሰረታዊ የጤና አገልግሎት በተለይም የእናቶች እና ሕጻናት ክትትል፣ የኤች አይ ቪ (ኤድስ) እና መሰል መሠረታዊ የጤና ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም በቋሚ ኮሚቴው አባላት ተጠቁሟል፡፡ የጤና መሠረተ ልማት ግንባታ ችግሮች እየተለዩ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ መፍትሔ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየቤተ ክርስቲያኗ ከ400 በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
Next articleአመልድ ለ256 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡