
አዲስ አበባ: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን ዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።
እ.ኤ.አ በ2024 በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ነጥብ 8 ሚሊዮን አዋቂዎች እና 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕጻናት በደማቸው ውስጥ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ እንደሚገኝባቸው ከጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሀገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎችን የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ ነው። ቅንጂታዊ አሠራርን በማጎልበትም ማኅበረሰቡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በቅንጅት በመሥራት በሽታው በማኅበረሰቡ ጤና እና ሰብዓዊ ደኅንነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየተሠራ እንዳለም ተመላክቷል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን ዘላቂነት ከማረጋገጥ አንጻር ችግሩን ከሥር መሠረቱ መፍታት እና የኤች አይ ቪ ኤድስ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም በትኩረት የምንሠራው ቀዳሚ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በኅብረተሰቡ ውስጥ ለቫይረሱ መስፋፋት የሚሰጠው ግምት እያነሰ መምጣት በተለይም አፍላ ወጣቶች እና ወጣት ሴቶች አሉታዊ የአቻ ግፊትን አለመቋቋም፤ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መኖር እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ለቫይረሱ ተጋላጭነት ቀዳሚ ጉዳይ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
ቫይረሱን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት አመርቂ መኾናቸውን ነው የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዲዔታው ዶክተር ደረጀ ድጉማ። እንደ ሀገር የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት ለመፍታት እና ውጤት ለማስመዝገብ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለም አመላክተዋል።
ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል በሚሠራው ተግባር ውስጥ የጤና ተቋማት የማይበገር የጤና ሥርዓትን በመዘርጋት የሚዲያ እና የሃይማኖት ተቋማት ሥራውን የጋራ አጀንዳ በማድረግ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ጤናማ ማኅበረሰብ የመፍጠር ሥራው ላይም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
