
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በተቋማዊ ሪፎርም፣ አፈፃፀም፣ ጂኦ ስትራቴጂካዊ እና በፖሊስ መሪነት አቅም ግንባታ ዙሪያ በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለሚገኙ የፖሊስ መሪዎች እና አባላት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሽት ሰላም እና ደኅንነነትን በማረጋገጥ ረገድ የፖሊስ አባላት ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን ያከናወኑት ተግባር ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው በነበረው የሰላም እጦት ውስጥ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ የፖሊስ አባላት ከፍተኛ ተጋድሎ ፈጽመዋል ነው ያሉት።
ተቋሙ በአዲስ መሪ እና ሙያዊ ሥርዓት ባለው አባል ሰላም እና ደኅንነትን ከማስጠበቅ ባሻገር የልማት ዘብ በመኾን የተለያዩ ሥራዎች እያከናወኑ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አበበ ውቤ ተናግረዋል።
ለፖሊስ አባላት የሚሰጠው ሥልጠና ሙያዊ አቅማቸውን ይበልጥ የሚያሳድጉበት መኾኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ አባላት በሥልጠና የሚያገኙትን ግብዓት በመውሰድ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ እንዲኾኑ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
