
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ ”ትውልድን በሥነ ምግባር፤ ተቋምን በአሠራር” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ይከበራል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመታገል በዓሉ በተለያዩ ኹነቶች እንደሚከበር ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በሥነ ምግባር ግንባታ፣ በግንዛቤ ፈጠራ፣ ሀብት በመመዝገብ እና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ላይ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ጥቆማዎችን በማጣራት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 43 ሚሊዮን ብር ከምዝበራ ማዳኑን እና 4 ሺህ ካሬ መሬት ማስመለሱን ገልጸዋል።
ሀብት ካስመዘገቡ 18 ሺህ 700 ሰዎች መካከልም በ200ዎቹ ላይ የማጣራት ሥራ ተሠርቷል። 20 ሰዎች ላይ ደግሞ ተጨማሪ ምረመራ እንዲደረግ ለፖሊስ ተልኳል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባር 2 ሺህ ካሬ መሬት እና 2 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ዲጂታል መታወቂያ፣ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የመሬት ካዳስተር ሥርዓት፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በስልትነት እየተሠራ መኾኑንም በአብነት ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነር ሞገስ በዓሉ በትምህርት ቤቶች እና በተቋማት የሥነ ምግባር ግንባታ እና ግንዛቤ ፈጠራ በመሥራት እንደሚከበር ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቶች በጥያቄ እና መልስ፣ በስፖርታዊ ውድድሮች እና በሌሎችም ሁነቶች ይከበራል ነው ያሉት። በመሥሪያ ቤቶች ደግሞ በውይይት ይከበራል ብለዋል።
የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ፣ ሙስና እንዳይፈጸም መከላከል፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ የሲቪክ ማኅበራትን ማጠናከር፣ በሙስና ላይ ሕግ የማስከበር እና በትብብር እና በቅንጅት መሥራት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መኾቸውን አብራርተዋል፡፡
የጸረ ሙስና ቀንን ከማሰብ ባለፈ ሙስና የሚያስከትለውን ሁለንተናዊ ችግር በመገንዘብ ሁሉም ለጸረ ሙስና ትግሉ የበኩሉን እንዲወጣ ነው ኮሚሽነር ሀብታሙ በመግለጫቸው ያሳሰቡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
