ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ ያለው መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ ነው።

7
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ)‎ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዓለም አቀፍ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
በዓሉ በየዓመቱ ኅዳር 22 ቀን የሚከበር ሲኾን የዘንድሮው በዓል” ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው የሚገኘው።
‎ዕለቱን አስመልክቶ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የፓናል ውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
‎የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱል ከሪም መንግሥቱ የጤና ፖሊሲ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል እና መቆጣጠር ዋናው ነው ብለዋል።
‎ኤች አይ ቪ ኤድስ አምራች ኃይሉን የሚጎዳ በሽታ በመኾኑ በትኩረት የሚሠራበት እንደኾነም ገልጸዋል።
‎በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሕክምና አገልግሎቶች እየተሰጠ ነው ብለዋል። የሥርጭት መጠኑ አሁን ላይ እንደ ክልል1ነጥብ1 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። በፊት ከነበረው የቀነሰ ቢኾንም ከፍተኛ መዘናጋት እንዳለ ይስተዋላል ነው ያሉት።
‎በሽታው በአብዛኛው ሴቶችን እና ወጣቶችን እያጠቃ መኾኑን ነው የተናገሩት። አሁንም ቢኾን በየዓመቱ በክልሉ ከ3 ሺህ 400 በላይ ሰዎች በአዲስ ይያዛሉ ነው ያሉት። ይህ የሚያመላክተው የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ውስንነት መኖሩን እንደኾነ ነው ያነሱት።
‎ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኤች አይ ቪ ኤድስን ከቤተሰቡ እና ከማኅበረሰቡ ነጻ ለማድረግ ግንዛቤን የማሳደግ ሥራ በባለቤትነት ሊሠራ እንደሚገባ አሰገንዝበዋል።
የ‎ማኅበረሰቡ ተመርምሮ ራሱን የማወቅ ልምድ ያልዳበረ በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ነው ያሉት። ለዚህም ሚዲያን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ማበርከት አለባቸው ብለዋል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአስር የተተከሉ ከሳተላይት ያለማቋረጥ ዳታ የሚቀበሉ ጣቢያዎች ወይም CORS ሥራ ጀመሩ።
Next articleሙስናን ለመከላከል የሁሉንም አካላት ትብብር ያስፈልጋል።