
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንት ውድድር በኦንላይን እየተካሄደ ነው። በውድድሩ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ትገኛለች። 200 ሀገራት በውድድሩ ተሳታፊዎች ናቸው።
የሥራ ፈጠራ ሳምንት መርሐ ግብሩ ዜጎች ክህሎታቸውን እና ችሎታቸውን መሠረት አድርገው ለፈጠራ እንዲዘጋጁ የሚያስችል የሥራ ምኅዳር መፍጠርን ዓላማ ያደረገ መኾኑን የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ገልጸዋል።
የፈጠራ ሳምንት ውድድሩን መሠረት በማድረግ በአማራ ክልል ለ103 ሺህ ዜጎች የሥራ ፈጠራ ሥልጠና መሠጠቱንም ኀላፊው ገልጸዋል።
የአደጉ ሀገራት የዕድገታቸው መነሻ ለፈጠራ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ኢትዮጵያም ሀገር በቀል እውቀት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት የክልል ፕሮግራም አስተባባሪ ይበልጣል ኤሊያስ እንደገለጹት ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንትን መሠረት በማድረግ በአንድ ሳምንት 103 ሺህ ለሚኾኑ ወጣቶች አጫጭር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 236 የሚኾኑት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ከ3 ሺህ በላይ የሚኾኑ ኢንተርፕራይዞችን ደግሞ ከባንኮች ጋር በማገናኘት የብድር ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። በየዞኑም ውይይቶችን ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።
የወጣቶችን የሥራ ፈጣሪነት አቅም ለማሳደግ ኮሌጆች ብቃት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። በሥራ ፈጠራ ሂደት ውስጥ የሚመለከታቸው ተቋማትም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የተሰጠው ሥልጠና ይበልጥ ለሥራ የሚያነሳሳ እና ትውውቅ የሚፈጥር መኾኑን በሥልጠናው የተሳተፉ ወጣቶች ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
