
ቅርሶቹን ለመታደግ የተጀመረው የሙዚዬም ግንባታም በበጀት ምክንያት ተቋርጧል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዓጼ ቴዎድሮስ የንግሥና ቦታ ደረስጌ ማሪያም ተጀምሮ የቆመው የሙዚየሙ ግንባታ ተጠናቀቆ ሥራ እንዲጀምር ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
ዘመነ መሳፍንት መቋጫ ያገኘባት፣ የኢትዮጵያ አንድነት የታወጀባት፣ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ከመንገሣቸው በፊት ደጃች ውቤን ቧሂት ከሚባል ቦታ ድል አድርገው ደጃች ውቤ ለንግሥና ባዘጋጁት የንግሥና ቦታና ዕቃዎች ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሡባት ቦታ ናት፤ ደረስጌ ማሪያም።
በ1682 ዓ.ም እንደተመሠረተች የሚነገርላት ቤተ ክርስቲያኗ ለዘመናት ጥበብ ያረፈበት የሕንጻ አሻራ ሳይደበዝዝ ውበቷ እንደጠበቀ ትገኛለች። ይሁን እንጅ በውስጧ የሚገኙ ቅርሶቹ በቤተ ክርስቲያኗ ዕቃ ቤት በተለመደው መንገድ በአንድ ላይ ተጫጭነው በመቀመጣቸው ለጉዳት ተጋልጠዋል። ችግሩን ለመፍታት በ2011 ዓ.ም የሙዚየም ግንባታ ቢጀመርም መቋረጡን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ነግረውናል።
የደረስጌ ማሪያም ቀበሌ ነዋሪው አቶ ገንታው ማሩ እንደገለጹት ቤተ ክርስቲያኗ በርካታ ቅርሶችን የያዘችና ያልተዘመረላት ናት፤ ታሪካዊ ቅርሶች በብዛት ቢኖሯትም በነዋሪዎች ስጋት ምክንያት ለጉብኝት ክፍት ሳትሆን ቆይታለች። በዚህም ምክንያት የአካባቢውን ማኅበረሰብና ቤተክርስቲያኗ ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ አጥተው ቆይተዋል።
በዚህ ወቅት አካባቢው ለጉብኝት ክፍት እንዲሆን ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት ላይ ቢደረስም ቅርሶቹ በባህላዊ መንገድ በአንድ ላይ ተደራርበው እና ተጫጭነው በመቀመጣቸው ለጉብኝት አመች አለመሆናቸውንም ነግረውናል። ቅርሶቹ አሁን ካሉበት አቀማመጥ ወጥተው በዘመናዊ መንገድ እንዲቀመጡ እና ለጉብኝት ክፍት ብቻ ሳይሆን ምቹም እንዲሆኑ ተጀምሮ የቆመው የሙዚየም ግንባታ ተጠናቀቆ ወደ ሥራ እንዲገባም ጠይቀዋል።
የደረስጌ ማሪያም አስተዳዳሪ አፈ መምህር ፈንቴ መንግሥቴ እንደገለጹት ቤተ ክርስቲያኗ በርካታ ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ይዛለች። ደጃዝማች ውቤ ለቤተ ክርስቲያኗ ያበረከቷቸው የብር እና የወርቅ ከበሮ፣ የብር እና የወርቅ መስቀሎች፣ የነሀስ፣ የብርና የወርቅ አክሊል እና ጽዋ በውስጧ ይገኛሉ። ይሁን እንጅ ቅርሶቹ በተደራጀና በዘመናዊ መንገድ ባለመቀመጣቸው ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ነግረውናል።
ይህን ችግር ለመፍታት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2011 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የሙዚየም ግንባታ አስጀምሯል፤ ነገር ግን በዚህ ወቅት ግንባታው ቆሟል።
የጃናሞራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አማረ ታደሰ እንደገለጹት ቤተ ክርስቲያኗ ከ400 በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በውስጧ ይዛለች። ‘‘እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ተጠብቀው የቆዩት በዘመናዊ መንገድ ሳይሆን በባህላዊ መንገድ በኬሻ ተቋጥረው በመደብ አንድ ላይ ተጫጭነው ተቀምጠው ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቤተ ክርስቲያኗን የሚመጥን ሙዚየም በ2011 ዓ.ም ግንባታ አስጀምሯል’’ ብለዋል አቶ አማረ። ይሁን እንጂ በበጀት እጥረት የሙዚየሙ ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ፍላቴ የሙዚዬሙ ግንባታው በበጀት እጥረት መቋረጡን ነግረውናል።
ተቋራጩም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሥራውን ማቋረጡን ገልጸዋል።
ሙዚዬሙ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተው ቀሪ ሥራውንና ሊጨርስ የሚችለውን በጀት መለዬታቸውን እና ጥናቱም የጋራ ከተደረገ በኋላ በቅርቡ ሥራው እንደሚቀጥል አቶ ኃይለየሱስ ተናግረዋል።
የጃናሞራ ወረዳ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከሚገኝባቸው ወረዳዎች መካከል ነው፤ በርካታ ገብኝዎች ወደ ፓርኩ ይሄዳሉ፡፡ ወረዳው ከፓርኩም ውጭ ደረስጌ ማርያም፣ ሰረባር ባለእግዚአብሔር ቅድመ ላልይበላ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን፣ የአባ ማርቆስ እና የአባ ሐን ጻድቃን የዋሻ አብያተ ክርስቲያናት፣ የቤተ እስራኤላውያን መካነ መቃብሮች፣ ክምር ድንጋዮችና የአምልኮ ቦታዎች መገኛም ነው፤ እነዚህን ሁሉ ሀብቶች በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ሀብት ተጠቃሚ በመሆን ግን ከዚህ ግባ የሚባል ሥራ ያልተሠራበት ጭምር ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
