
ደብረ ታቦር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አሕጉር አቀፍ የደም ልገሳ ፕሮግራምን “አንድ ቀን፣ አንድ አሕጉር፣ አንድ ዓላማ” በሚል መሪ መልዕክት ዘመቻ አካሂዷል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ደም እና ኅብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት አሥተባባሪ እና የደም ባንክ ባለሙያው መላኩ ምስጋናው እንደ ክልል 800 ከረጢት ደም እና እንደ ደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ደግሞ ከ50 ከርጢት በላይ ደም ለማሰባሰብ አቅደው እየሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።
አቶ መላኩ ከሙያዊ ኀላፊነታቸው በተጨማሪ ደም ለ59ኛ ጊዜ በመለገስ ሰብዓዊነታቸውን እየተወጡ ስለመኾናቸውም ነግረውናል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደም መለገስ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የለውም ብለዋል።
ሊቋርጥ የነበረን ሕይዎት ማስቀጠል መቻል ልዩ ስሜት አለው፤ ደም መለገስ ለራስም ጤና የሚመከር እና አዕምሯዊ እርካታው ከፍተኛ የኾነ ነው ብለዋል። ደም መለገስ ማኅበራዊ ኑሮንም ያስተሳስራል ነው ያሉት።
ደም በመለገስ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን እና በኛ ደም ሰዎቹን ማዳን ስለሚቻል የበኩላችን ኀላፊነት መወጣት አለብን ብለዋል።
ራስን ሳይጎዱ የሌሎችን ሕይዎት የምንታደግበት እና በዚህ ምድር ላይ ካሉ ስጦታዎች ሁሉ የላቀው ትልቁ ስጦታ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ወጣቶች ናቸው። ሕይዎትን የመታደግ መልካም እና ፍጹም ሰብዓዊነት ያለው ተግባር መኾኑን ነው የገለጹት።
ለሁለተኛ ጊዜ ደም በመስጠት ላይ ያገኘነው ወጣት ሀብተማርያም ብረሃን ደም ለመለገስ ያነሳሳው ጉዳይ በደም እጦት የሚሞቱ ሰዎች ግንዛቤው ስላለኝ ነው ይላል። ደም በመለገሱ ደሰተኛ እንደኾነም አጫውቶናል።
ተማሪ አማኑኤል መሳፍንት ደግሞ ለስምንተኛ ጌዜ ደም በመለገስ ላይ ነው ያገኘነው። ደም መለገስ የሚቀንስብኝ ነገር የለም፤ በደም እጦት አንድት እናት ሕይዎቷ አደጋ ላይ እንደነበር ባጋጣሚ ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ በየሦስት ወሩ ደም መለገሴን ቀጥያለሁ አለን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
