ተደራጅተው ኅብረተሰቡን ሲዘርፉና ሲያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

66
ባሕር ዳር: ሕዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኅብረተሰቡ ጥቆማ በመከላከያ ሠራዊት ከ101ኛ አየር ወለድ ክ/ጦር 2ኛ ንስር ሻለቃ በተጠና መረጃና ክትትል ሕዳር 14/2018 ዓ.ም በባሕርዳር እና አካባቢዋ ዘራፊዎቹ ከያሉበት ተይዘው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን የምሥራቅ ዕዝ ሚዲያ አስታውቋል፡፡
ዘራፊ ቡድኖቹ አበባው አፈወርቅ በተባለው ግለሰብ ስምሪት ሰጭነት በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ባለሀብቶችን ስልክ ቁጥር በማፈላለግ እየደወሉ ብር ካላስገባችሁ ከነ ቤተሰቦቻችሁ እንገላችኋለን እያሉ ብር ሲዘርፉ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
አባላቱ ሕገ ወጥ ማህተም በማስቀረፅ፣ ስማቸውን በመቀያየር፣ በሀሰተኛ ስም አካውንት በማውጣት ኅብረተሰቡን ሲዘርፉ ቆይተዋል።
ከተያዙት ዘራፊዎች መካከል
1. አበባው አፈወርቅ የተባለ ዋና ስምሪት ሰጭ፣
2. ተካልኝ እውነቴ፣ ሐሰተኛ ማህተም አስቀርፆ ብር እየተቀበለ መታወቂያ ሲሰጥ የነበረና ፎርጅድ አስር ሺህ ብር እየተቀበለ በትክክለኛ ሁለት ሺህ ብር ሲቀይር የነበረ፣
3. ደሳለኝ አሰፋ ፣ የገበሬውን በግ ገዛሁ እያለ በሞባይል አካውንት ያስገባ በማስመሰል ሲያጭበረብር የነበረ
4. መብቱ ታረቀኝ፣ ስልክ እየደወለ በማስፈራራት ብር አስገቡ እያለ ሲያታልል የነበረ፣
5. ታረቀኝ ይርዳው ፣ የሚዘረፍ የባለሀብት ስልክ አፈላላጊ ፣ ወንድሙ እንዲዘረፍም ስልክ የሰጠ ይገኙበታል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ባለሀብቶች ቀያቸውን ለቀው እንዲሸሹና ሕዝቡም እንዲማረር ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡
ሕብረተሰቡ እንደነዚህ ዓይነት ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈፀም ለአካባቢው የፀጥታ አካላት ጥቆማውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቁሟል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ወልቃይት እንግዳ አልምዶ የሚያስቀር ድንቅ ምድር መኾኑን በአካል አየሁ” ዳኛቸው አሰፋ (ዶ.ር)
Next articleሊቋርጥ ነበረን ሕይዎት ማስቀጠል መቻል ልዩ ስሜት አለው።