“ወልቃይት እንግዳ አልምዶ የሚያስቀር ድንቅ ምድር መኾኑን በአካል አየሁ” ዳኛቸው አሰፋ (ዶ.ር)

25
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ምድሩ የተከዜ ዳር የውበት ሰገነት ነው” ብለውታል በቅርቡ ወደ ቀጣናው ዘልቀው ጉብኝት ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አስፋ። ዕውነት ነው፤ ወልቃይት ቢጓዙት የማያልቅ ሜዳማ፣ ቢያዩት የማይሰለች ባለአረንጓዴ መልክ፣ የእነ ቲፋሻ ፏፏቴ መገኛ፣ የቤተሞሎ ጥንተ ርስት እና የነጭ ወርቅም መብቀያም ነው።
ሰዎቹም በፍቅር እና በአንድነት አማኝ፣ በአማራዊ እና ኢትዮጵያዊነት ከፍታ የቆሙ፣ በችግር ቢፈተኑ እንኳን ላመኑበት ዕውነት ዋጋ ከፍለው እና በጽናት ከፍ ብለው ቆመው የታዩ ናቸው። ለልማት እጃቸው የማይታጠፍ፣ ሰላም ወዳድ፣ ሁነኛ የሀገር ዘብ፣ አትንኩኝ ባይ፣ ሰው አክባሪ እና እንግዳ አቀማጣይ ናቸው ይላሉ ዶክተር ዳኛቸው።
ወደ አማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ማቅናታቸው የሕዝቡን አኗኗር እና የልማቱንም ውጤት ለመመልከት ዕድል እንደሰጣቸው አብራርተዋል።
“ወልቃይቴዎች ለአካባቢያቸው፣ ለክልላቸው እና ለኢትዮጵያም ጭምር ሰላም መኾን እየታተሩ ያሉ የሀገር ማገር መኾናቸውን በአካል አይቸ ተመለስኩ” ነው ያሉት ዶክተር ዳኛቸው።
ችግሮች ያጠነከሩት እንጅ ያልበገሩት፣ በአለት ላይ የተገነባ የሥነ ልቦና ልዕልና ያለውን ሕዝብ በዐይኔ አይቸው መጣሁ ሲሉም ገልጸዋል። ‘ራሴን እየጠበቅሁ አለማለሁ’ ብሎ የተነሳ፤ እውነትም ሰላሙን በአስተማማኝነት የጠበቀ እና በገፍ የሚያለማ ሕዝብ በመመልከቴ ደስ ብሎኛል” ነው ያሉት።
“ለሕዝብ እና ለሀገር ልዕልና ወሳኙ ነገር መሪ ነው” የሚሉት ዶክተር ዳኛቸው መሪውን ያከበረ፣ ያዳመጠ፣ ቀርቦ እያገዘ ክፍተቶቹን የሞላ እና ያጀገነ ሕዝብ ሰላሙን ያስጠብቃል፣ ልማቱንም ያፋጥናል ብለዋል።
ሕዝብ መሪዎቹን ሲያዳምጥ፣ በየደረሱበት በስስት እያቀፈ እና ወደቤቱ እየጋበዘ ሲያጎርስ፣ ከመንግሥት የተጓደለበትን ደግሞ በጨዋነት ቁጭ ብሎ ሲጠይቅ፣ ሕዝብ እና መሪ ይተሳሰራል፣ ልማትም ይሰምራል ነው ያሉት። ይህንን አይነቱ የመሪ እና የሕዝብ የጠበቀ ቁርኝት ወልቃይት ላይ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ሕዝቡ ሀገር ወዳድ እና ከአካባቢው እስከ ሀገሪቱ ያሉ መሪዎቹን አክባሪ መኾኑ ለአካባቢው ሰላም እና ልማት ልዩ ዕድል ሰጥቷል ባይ ናቸው የፍልስፍና መምህሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደሁመራ ከተማ በአዲስ የጀመረውን በረራ ተከትሎ ወደቦታው እንዳቀኑ እና አካባቢውን በሙሉ ተዘዋውረው መመልከታቸውንም ተናግረዋል።
የወልቃይት ሕዝብ በደስታ ነው የተቀበለን፣ የእንግዳ አቀባበል ለዛ እና እሴቱ በቃላት የሚገለጽም አይደለም ብለዋል።
ዶክተር ዳኛቸው “ወልቃይት ላይ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተመለከትኩ፤ እነሱም ፍቅር፣ መከባበር እና ጀግንነት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል። የአካባቢው ሕዝብ ፍቅርን ብቻ የሚያስቀድም ነው፣ ለሰው ልጆች ሁሉም ክብር ይሰጣል ብለዋል።
ወልቃይት ላይ የታለፉ ችግሮችን መርሳት እና መዘናጋት ብሎ ነገር የለም፤ በሕዝብ የተጠናከረ አቅም እና ብርቱ ወኔ አካባቢ እና ሀገር በንቃት እየተጠበቀ ነው፤ ይህም የሥልጡንነት አንዱ መገለጫ ነው ብለዋል ዶክተር ዳኛቸው።
በሕዝቡ አማራዊ ማንነት ላይ አተኩረው የደረሱ በደሎች ለቂም በቀል እንዲውሉ ሳይኾን እንዳይደገሙ ለማስተማር የሚነሱበት፣ ራስን እና ሀገርን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት የሚሠራበት አካባቢ ስለመኾኑም ገልጸውልናል።
ሀገሬን እና የውጩን ዓለምም በብዙው አውቃለሁ፣ ወልቃይት ላይ ግን የበለጠ እንዳጠና የሚጋብዙ ውብ ባሕሎች ተመልክቻለሁ ነው ያሉት ዶክተር ዳኛቸው። የቀየው ሰዎች እንግዳ አቀባበል፣ ክብር አሰጣጥ፣ የምግባቸው አሠራር፣ አቀራረብ እና ጣዕም ሁሉም ልዩ መልክ ያለው ነው ብለዋል። “ወልቃይት ዕውነትም እንግዳ አልምዶ የሚያስቀር የውብ ባሕል ባለቤት ድንቅ ምድር መኾኑን በአካል አየሁ” ነው ያሉት ዶክተር ዳኛቸው።
“አሁን ሕዝቡ በነጻነት እና በእፎይታ ውስጥ ነው” ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ሰላም እና ልማት የሰፈነበት ስለመኾኑም ትዝብታቸውን ገልጸዋል። ሁመራን፣ ዳንሻን እና ሌሎችንም ከተሞች እና የገጠሩን የልማት አካባቢ ተዘዋውረው ስለመመልከታቸውም ተናግረዋል።
ሕዝብ እየተባበረ በትናንሽ ከተሞች ላይ ጭምር የተጀማመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፎች እና ሌሎች ልማቶች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ታዝበዋል።
“ወልቃይት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካም የተስፋ ምድር ናት” ሲሉም ገልጸዋል። የሰፋፊ እርሻዎች ምድር፣ የነጭ ወርቅ መብቀያ፣ የጥጥ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎችም አውድማ መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የሕዝቡ ፍቅር፣ መተሳሰብ እና ኢትዮጵያዊ አንድነት የልማቶች ሁሉ እርሾ ስለመኾኑ አብራርተዋል።
ሕዝቡ ያገኘው ነጻነት በሕግ ጭምር ሲጸናለት አሁን የሚታየው ሰላም ዘላቂ ይኾናል፤ ሁሉም በፍቅር የሚኖርበት እና ልማት የበለጠ የሚያብብበትም ቀጣና ይኾናልም ብለዋል ዶክተር ዳኛቸው ።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሀዘን ቤት ወይስ ቁማር ቤት?
Next articleተደራጅተው ኅብረተሰቡን ሲዘርፉና ሲያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡