
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስለምን መልካም እሴቶቻችንን እና ነገሮቻችንን ጥላሸት እንቀባቸዋለን? ስለምንስ ኹሉን ነገር ድሮ ቀረ የሚል ትውልድ እንፈጥራለን?
ሀገራችን ውስጥ በሌሎች ሀገራት የማይገኙ ብርቅዬ እንስሳት ብቻ ሳይኾኑ ብርቅዬ እሴቶችም በብዛት አሉን። እነዚህን እሴቶች ለመጠበቅ የሚጥሩ ባይጠፉም በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ለመናድ የሚሯሯጡት ግን ተበራክተዋል ባይ ነኝ።
እነዚህ ብርቅዬ እሴቶቻችን ከኛ ጋር ወደ ሌሎች ሀገራት እየተሰደዱ ባይኾንም በኛው ሀገር ውስጥ ከስመው እንዳይጠፉብን ሁላችንም መጠንቀቅ አለብን እላለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት እና አኹንም ያሉት እንደ ዕቁብ፣ እድር፣ ሠርግ፣ ደቦ፣ አፈርሳታ፣ አውጫጪኝ፣ አበጋር፣ ሽምግልና፣ አቆልቋይ እና መሰል ብርቅዬ እሴቶቻችን ዛሬ ላይ የነበራቸውን ወዝ እና ቁመና ይዘው እየቀጠሉ ስለመኾኑ እጠራጠራለሁ፡፡ በዛሬው ትዝብቴ በዕዝን ላይ ያስተዋልኳቸውን ጥቂት ነገሮች ብቻ ላድርሳችሁ፡፡
ብዙዎቻችን የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንን ወይም ሌሎች ሰዎችን በድንገተኛ አደጋም ይሁን በሕመም፣ በሞት ስናጣቸው ከፍተኛ ሀዘን ላይ እንወድቃለን፡፡ ያም ኾኖ ግን ሞት ተፈጥሯዊ ጉዳይ በመኾኑ ቀስ በቀስ መጽናናታችን አይቀሬ ይኾናል፡፡
በኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ እድር ያሉት የመረዳጃ ማኅበራት ደግሞ ሀዘንን ለማቅለል ዓይነተኛ የሥነ ልቦና ሕክምና መስጫዎቻችን ናቸው፡፡ በእጅጉ የምንወዳቸውን ወይም የመኖራችን መሠረት የኾኑ ሰዎችን ከአጠገባችን ስናጣ በአጠገባችን የሚገኙት የእድር አባላት ወይም ሌሎች አስተዛዛኞቻችን ለመጽናናታችን ሚናቸው የላቀ እንደኾነ ሀዘን የደረሰበት ሰው ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡
በተጎጂው ቤተሰብ አቅራቢያ የሚተከለው ድንኳን በሦስተኛ ቀኑ እስከሚፈርስ ድረስ ሀዘንተኞችን የማጽናናቱ ተግባር በሌላው ዓለም ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለዕዝን እየተባሉ የሚመጡ ነገሮችን በጋራ ተቋድሶ ነፍስ ይማር እያሉ መሰናበቱም ለተጎጂዎች ተኪ የሌለው የሥነ ልቦና ሕክምና ነው፡፡
ይህ ብርቅዬ የማስተዛዘን እሴታችን አሁን ላይ መልኩን ቀይሮ የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ከኾነ ሰነባብቷል፡፡ ለሀዘን በተተከለ ድንኳን ውስጥ በዋጋቸው ኾነ በአልኮል ይዘታቸው ከፍተኛ የኾኑ የአልኮል መጠጦች እየገቡ ድንኳኑን የመሸታ ቤት ማስመሰላቸው መቼም ለሀዘንተኞቹ ይጠቅማቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ድንኳኑ ውስጥ ዳቢት ከሻኛ ሥጋ እያስመረጡ ወይም በቡፌ ምግብ ደርድሮ የለቅሶውን ቤት የደስታ ቤት ማስመሰሉም ቢኾን የኛ መልካም እሴት መገለጫ አይደለም፡፡ በሀዘን ቤት ውስጥ ከልክ በላይ ጠጥቶ፣ የጠጡትን በዓይናቸው እያነቡ ለሟች ያዘኑ መምሰልም አስመሳይነት እንጂ አዛኝነት ሊኾን አይችልም፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ድንኳን ባዩ ቁጥር ሮጠው በመግባት ቁማር መጫወትን ልማድ አድርገዋል፡፡ ሀዘንተኞችን ለማስተዛዘን ወይም ብዙ ሰዓትን አብሯቸው ለመቀመጥ ተብሎ የተጀመረው የድንኳን ውስጥ የካርታ ጨዋታ አኹን ላይ በሺህ ብሮች የሚቆመርበት መኾኑ ሲታይ ድንኳኖችን ሀዘን ቤት ወይስ ቁማር ቤት? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በየድንኳኑ ውስጥ ቁማር የሚጫወቱ ሰዎች የሟቹን ማንነት የማያውቁ ቁማርተኞች መኾናቸው ያስተዛዝባል፡፡ ሟቹ ወንድ ይኹን ሴት ሳይለዩ ድንኳኑ ውስጥ ገብተው ቁማራቸውን ይቆምራሉ፤ የእዝን ጥሬ ይዘግናሉ፤ የቀረበላቸውን መጠጥ ይጠጣሉ፤ ቁርስ፣ ምሣ እና እራታቸውን ይበላሉ፤ በቁማር ገንዘባቸው ከተበላ ደግሞ በሀዘንተኞቹ መኸል ይሰዳደባሉ፤ አለፍ ሲሉም የሚደባደቡ አሉ፡፡
ቁማር መጫወት ሕገ ወጥነት መኾኑን የተረዱት እነዚኽ ቁማርተኞች በየድንኳኑ ውስጥ መሽገው ሲቆምሩ መዋላቸው ሳያንሳቸው ተጣልተው በሀዘን ቤቱ ላይ ሌላ ሀዘን መጨመራቸውን አለመታዘብ አይቻልም፡፡ እነዚኽ ግለሰቦች ከሕግ የተደበቁ ሕገ ወጦች እንጂ ሀዘንተኞች አለመኾናቸውንም መረዳት ይኖርብናል፡፡
ብርቅዬ የነበረው የመተዛዘን እሴታችን ፈሩን እየለቀቀ ለሀዘን የሚተከሉት (የሚጣሉት) ድንኳኖች መስከሪያና መቆመሪያ ሲኾኑ ማየት በእጅጉ ያሳምማል፡፡ ይኽንን እየተበረዘ ያለ መልካም እሴት በጊዜ መልክ ካላሲያዝነው ወይም ወደነበረበት ጥሩነቱ ካልመለስነው በቀር መሞት ድሮ ቀረ…፣ ማዘን ድሮ ቀረ…፣ ሌሎች ነገሮችም ድሮ ቀሩ እንዳንል እሠጋለሁ፡፡ እናንተስ?
በእሱባለው ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
