
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርበኛው፣ ዲፕሎማቱ፣ ሀገረ ገዥው ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ በዚህ ሳምንት ኅዳር 15/1885 ዓ.ም ነው በሸዋ ጠቅላይ ግዛት የተወለዱት። ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ሀገራቸውን ከወረራ በመከላከል ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው።
በተለይም እ.ኤ.አ ከጥቅምት 1935 ጀምሮ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራን በመመከትም ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው። ራስ እምሩ ለአጭር ጊዜ የሰሜን እና የበጌምድር ጠቅላይ ገዥ ኾነው ከቆዩ በኋላ የዘውድ አማካሪ ኾነውም ተሹመው በሕንድ እና በአሜሪካ ሀገር በአምባሳደርነት አገልግለዋል።
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ሁልጊዜ የዘመናዊ እና የለውጥ አመለካከቶች አራማጅ ከሚባሉ ሰዎች መካከል የሚመደቡ እጅግ የተመሰገኑ ሰው ነበሩ። በተለይም እኒህ ሰው በኢትዮጵያ ዘመናዊነት እንዲሰፋ እና የሚሠሩ ሥራዎች ዘመናዊ እንዲኾኑ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰውም ናቸው። የመረጃ ምንጫችን ብላክ ላየን መጽሔት ነው።
አለቃ ታዬ ገብረማርያም ሀገራቸውን የሚወዱ ታላቅ ሰው ነበሩ። የሀገራቸውን ፍቅርም በተግባር የገለጡ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። እኒህ ሰው በዚህ ሳምንት ኅዳር 21/1853 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ አለቃ ታዬ የውጭ ቋንቋዎችን እና ሰፋ ያለ የታሪክ እና የሰዋሰው መጽሐፍትን ከላቲን፣ ከግሪክ እና ከዓረብ ቋንቋ አጥንተዋል፡፡
የነበራቸው ዕውቀትም ከታላላቅ ሰዎች ጋር አስተዋውቋቸዋል፡፡ አለቃ ታዬ በ1891 ዓ.ም ወደ ሸዋ ሄደው ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተርጉመው እና አስፋፍተው የጻፉትን የሰዋሰው መጽሐፍ ለአጼ ምኒልክ እና ለእቴጌ ጣይቱ ደነባ ላይ ተገኝተው አበርክተዋል፡፡
1896 ዓ.ም መጨረሻ የጀርመን ንጉስ ግዕዝ እና አማርኛ አጠናቅቆ የሚያውቅ የውጭ ቋንቋ የሚናገር ሰው ሲፈልግ ወደዛው ሄደው የሀገራቸው አምባሳደር በመኾን ሠርተዋል።
አለቃ ታዬ አውሮፓ በቆዩባቸው ጊዜያት ከኢትዮጵያ ተወስደው ጀርመን የሚገኙ 130 ቅርሶችን ዝርዝር ለአጼ ምኒልክ በመላክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ብዙ ጥረት ያደረጉ የሀገር ፍቅር ያላቸው ሰው ናቸው።
በ1912 ዓ.ም በተቋቋመው ካቢኒ ከተመረጡት ምሁርም አንዱ ኾነው በመንግሥት ሥራ ላይ ተሠማርተው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጲያ ሕዝብ ታሪክ የሚል መጽሐፍም አሳትመው ለንባብ ማብቃታቸውን ዘብላክ ላየን መጽሐፍ ከትቦት ይገኛል፡፡
ልክ በዚህ ሳምንት አሜሪካውያን የሚመሰጋገኑበት ቀን ያስፈልጋል በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጋና ቀን የታወጀበት ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን አሜሪካውያን ላገኙት አገልግሎት እና እርስ በርሳቸው ያላቸውን ክብር እና አድናቆት ይገላለጹ ዘንድ ትልቅ ፍላጎት ነበራቸው፡፡
ይህም በአሜሪካውያን ዘንድ ያለውን መተሳሰብ ከፍ ያደርጋል ብለው ያሰቡት ፕሬዝዳንቱ ቀን ተቆርጦለት ይከበር ዘንድ ያደረጉ መሪም ናቸው። ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ኅዳር 17/1782 ዓ.ም “የሕዝብ የምሥጋና ቀን” የሚል አዋጅ ማውጣትም ቻሉ፡፡ በአዲሱ ሕገ መንግሥታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ የምስጋና ቀን እንዲከበር ያደረጉ መሪ መኾን ችለዋል።
የአዋጁን መውጣት ተከትሎ እኔ ለዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ የምስጋና ቀንን እመክራለሁ ሲሉ ቀኑ ምን ያህል አስፈላጊ እና በዜጎች መካከል የሚፈጥረውን መልካም ወዳጅነት ስለመግለጻቸው ይነገራል፡፡
ለመኾኑ እኛስ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳችን ለተሰጠን አገልግሎት እና ድጋፍ እየተመሰጋገን ይኾን? ምሥጋና የሰላም ማሰሪያ ውሉ ነው እና አመስጋኞች እንሁን።
መረጃውን ላይቨራሪ ኦፍ ኮንግረንስ ከተሰኘ ድረ ገጽ አገኘን።
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
