
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከማድረግ ተሻግራ የተገቢነቱን ጉዳይ ለብዙዎች እያስረዳች ትገኛለች። የሀገሪቱ ታሪክ ሲነሳ በከፍታውም ይሁን በዝቅታው ወቅት የባሕር በር አብሮ የኖረ እርስቷ ነው።
ይህንን የባሕር በር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ላይ ያለ ልዩነት ለኢትዮጵያ እንደሚገባ ማሳየት ያስፈልጋል ይላሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሀሳቡ ተስፋ።
የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ጉዞ ታሪክ በቀጥታ ከባሕር በር ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ያለባሕር በር የኖረችበት ታሪክ ምናልባት ያለፉትን ሦሥት አስርት ዓመታት ካልኾነ በስተቀር የኢትዮጵያ የከፍታ ታሪክ ሲነሳ የባሕር በር አብሮ ይነሳል ነው ያሉት።
“የባሕር በር እየጠየቅን ያለነው የሀገረ መንግሥት ታሪካችን ያወረሰን ሃብታችን ስለኾነ ነው” ብለዋል። አሁን ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለችው ትላንት የራሷ የነበረውን እና እንዴት እንደተወሰደ ምክንያቱ በግልጽ የማይታወቀውን ሃብቷን እንደኾነ አስረድተዋል።
“ኢትዮጵያ ከባሕር ገሸሽ የተደረገችበት መንገድ ለኛ ለባለቤቶቹ ግልጽ አይደለም፤ ፍትሐዊም አይደለም” ነው ያሉት። በወቅቱ ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረትን ባልተከተለ አካሄድ ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትገፋ ተደርጓል ሲሉ አስረድተዋል። ይሄም ለመላው ኢትዮጵያውያን ግልጽ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን ፖለቲካዊ አመክንዮ ብቻ የሚሰጡ አካላት አሉ የሚሉት መምህሩ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው ብለዋል። በእርግጥ ኢኮኖሚም ይሁን ማኅበራዊ ፍላጎት በፖለቲካ ነው የሚመራው ያሉት መምህር ሀሳቡ ተስፋ ኢትዮጵያ ለፖለቲካ ለኢኮኖሚ እና ለማኅበራዊ ፍላጎት መሻቷ የግድ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት አስገንዝበዋል።
ቀጣናው የብዙ ኀይሎች የስዕበት ማዕከል ኾኗል ብለዋል። “ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ኀያላን ሀገራት ማዕከላቸው አድርገው የከተሙበትን ቀጣና በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተቀምጠን የምንገፋበት አንዳች ምክንያትም ኾነ ሕጋዊ መንገድም የለም” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ በሃሳብ ልንለያይ እንችላለን በሀገር ጉዳይ ላይ ግን የግድ በአንድ መቆም ይኖርብናል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ልሂቃን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት ይህ ጉዳይ ያለ ልዩነት የሚከናወን ተግባር መኾኑን መረዳት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
መንግሥትም በተጠና መንገድ ሥራዎችን በመሥራት ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን መንገድ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
