24 ዓመታትን በስህተት እስር ለማቀቀ ሕይወት ገንዘብ እፎይታ ይሰጥ ይሆን?

194

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) 24 ዓመታን በስህተት የታሰሩት ወንድማማቾች በካሳ መልክ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን አሜሪካ ዶላር ተሰጥቷቸዋል፡፡

ባልፈጸሙት የግድያ ወንጀል ተፈርዶባቸው ለ24 ዓመታት ወህኒ የኖሩት ወንድማማቾች ለእያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ለ24 ዓመታት በስር ከማቀቁ በኋላ ዐቃብ ሕግ የወንድማቾቹን የእስር ሁኔታ ድጋሜ በመርመር ነው ወንጀለኛ አለመሆናቸውን ያረጋገጠው፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረትም ኤሪክ ሲሞኒ እና ካንተዝ ጁኔር ባለፈው ዓመት ግንቦት ከእስር እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ የሁለቱ ወንድማማቾች ፍትሐዊ ያልሆነ እስር የአሜሪካ ፖሊስና የፍትሕ ሥርዓቱ ዘንፈት ታይቶበታል፡፡

እነዚህ የፈረደበት ጥቁር ቆዳ የለበሱ ወንድማማቾች በ1994 (እ.አ.አ) ነበር በምሥራቃዊ ባልቲሞር ሜሪላድ ውስጥ የ21 ዓመት ወጣት በመግደል ወንጀል የተከሰሱት፡፡ በውሸት ምሥክርና ባጋደለ ፍርድ ለ24 ዓመታት በእስር ማቀቁ፡፡ ፖሊስ ባዘጋጃቸው የሐሰት ምሥክሮች ተመሥክሮባቸው ነው ዘብጥያ የተወረወሩት፡፡
ከ24 ዓመታት በኃላ እውነት የተገለጠችለት የ49 ዓመቱ ኤሪክ ሲሞኒ ‘‘የሜሪላንድ ግዛት የመንግሥት ሠራተኞች ስላደረጉት ድጋፍ አደንቃለሁ፤ ነገር ግን ገንዘቡ ያለፈውን ጊዜ ፈጽሞ ሊተካ አይችልም’’ ብሏል፡፡ ሲሞኒ ይቀጥላል “እናቴ በእስር ቤት እንዳለሁ ሞታለች፤ በገንዘቡ እናቴንም ሐዘኔንም መመለስ አልችልም” ሲል ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል፡፡ ሲሞኒ የማረሚያ ቤት ጠባቂዎች ይደበድቡት እና ወደ ጉድጓዱ ውስጥ ይጥሉት እንደነበር አስታውሶ ገንዘብ ያንን ሊያስተካክለው እንደማይችልም ተናግሯል፡፡

ሲሞኑ ያን የመከራ እስር ቤት እያስታወሰ ወደቤቱ ከተመለሰ በኋላ “በየቀኑ ከእንቅልፌ እነሳና ‘እውነት ነው?’ ብዬ እጠይቃለሁ” ብሏል፡፡ እ.አ.አ በ2010 የተጠዬቀው ይግባኝ ውድቅ መደረጉ በሕይወቱ ላይ ታላቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረበትም ተናግሯል፡፡ “የእኔ ውሳኔ ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ መነሳት አልፈልግም ነበር፡፡ በሰውነቴ ውስጥ እስትንፋስን ያወጣው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲልም ምሬቱን ተናግሯል፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች በተሳሳተ ፍርድ ካሳ ሲቀበሉ 9ኛ እና 10ኛ ሰዎች ናቸው፡፡ በግዛቷ በሐሰት ለዘብጥያ የተዳረጉ ብዙ ናቸው፤ የተካሱት ግን ጥቂት ናቸው፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት ለሚገኙ ሰዎች መጻሕፍት ተበረከተላቸው።
Next articleየቤተ ክርስቲያኗ ከ400 በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡