የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

13

አዲስ አበባ: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከ5ሺህ 500 በላይ በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የተመዘገቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይገኛሉ።

ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል ከ3ሺህ 500 በላይ የሚኾኑት በሥራ ላይ የሚገኙ ናቸው። ከ300 በላይ የሚኾኑት ደግሞ በሀገሪቱ በሰላም ግንባታ ዘርፍ ተሳትፎ እያደረጉ መኾናቸውን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ የግጭት ምንጮችን በመለየት ግጭትን ለመፍታት የሚሠሩ ድርጅቶች በርካታ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ በሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ካላቸው ብዛት አንፃር በሰላም ግንባታ ዘርፍ በስፋት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ.ር) መንግሥት ግጭቶችን ለማስቆም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን አንስተዋል።

የግጭት ምንጮችን በጥናት መለየት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እና ግጭቶችን ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለሰላም ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በሰላም ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በተለያየ መንገድ ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን የሃይማኖት አባቶችን፣ የጎሳ መሪዎችን እና አባገዳዎችን በመጠቀም ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ግጭቶች እንዲቆሙ ማድረግ መቻላቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ተመሥገን ዳረጎት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የችሮታ ጉዳይ ሳይኾን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው።
Next articleየባሕር በር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት ሊቆሙ ይገባል።