
ጎንደር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ በቆዳ ስፋት እና በሕዝብ ብዛት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የኾነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ካጣች ሦሥት አሥርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች።
ኢትዮጵያ የኤርትራን ሀገር መኾን ተከትሎ ከባሕር በር ከተገለለች በኋላ ታሪካዊ ይዞታዋን ተነፍጋ ለገቢ እና ወጭ ንግድ የጂቡቲ ወደብን እየተጠቀመች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ለጂቡቲ ወደብ የምታወጣው ወጭ ለሀገር ልማት ማዋል ቢቻል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይቻል እንደነበር ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ከተማ የፋሲለደስ ቁጥር ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር አሰፋ አገዘ ገልጸዋል።
የታሪክ መምህሩ አሰፋ አገዘ ኢትዮጵያ በአክሱም ዘመነ መንግሥት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ በተንሰራፋው ውኃማ አካላት ላይ አዱሊስ፣ በርበራ፣ ዘይላ፣ መረካ እና መቋዲሾ የመሰሉ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች ያነሳሉ።
መምህር አሰፋ እንደሚሉት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ገናና መንግሥታት መካከል የአክሱም ነገሥታት አንዱ እንደኾነም አስረድተዋል።
ለወቅቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ገናናነት ደግሞ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር እና አካባቢውን ተቆጣጥራ ንግዷን ማሳለጧ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነት ከተነጠለች በኋላ ከሥነ ልቦና ስብራት እስከ ኢኮኖሚ ድቀት እንዳጋጠማትም መምህሩ ያነሳሉ።
የባሕር በር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መስፈንጠር ዋነኛ መንገድ መኾኑን መገንዘብ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል ሲሉም አሰገንዝበዋል።
አሁን ላይ ያለው የምሥራቅ አፍሪካ እና አካባቢው ጂኦ-ፖለቲካል ውጥረት አካባቢውን ለመቀራመት እና የራሳቸውን ዕድገት ለማፋጠን መኾኑን መገንዘብ ሌላው ከኢትዮጵያውያን እንደሚጠበቅ የታሪክ መምህሩ አስረድተዋል።
ሌላኛው በጎንደር ከተማ የፋሲለደስ ቁጥር ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር አደገ ጌታሁን ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስትጀምር የዓለም አቀፍ ተቋማት ተቃውሞን አስተናግዳ እንደነበር አስታውሰዋል።
መምህሩ ይደርስ የነበረውን ተቃውሞ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በተደረገው ጥረት የሕዳሴ ግድቡ በስኬት ሊጠናቀቅ መቻሉንም አመላክተዋል።
“ይህን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የታየውን ጠንካራ ዲፕሎማሲ ማስቀጠል እና በባሕር በር ላይም መድገም ይገባልም”ይላሉ የታሪክ መምህሩ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የችሮታ እና የልመና ጉዳይ ሳይኾን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ መኾኑንም አስረድተዋል።
መምህሩ ኢትዮጵያ ገናና በነበረችበት ዘመን ቀይ ባሕር እና አካባቢው የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ አካል እንደነበሩ የታሪክ ማሳያዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
ለዚህም እነ ዞስካለስ፣ አምደ ጽዮን፣ ሰርፀ ድንግል፣ አክሊሉ ሐብተ ወልድ፣ ዘውዴ ረታ እና ሌሎች የታሪክ ጸሐፍት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች ምስክር መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
