በከሚሴ ከተማ በመልሶ ማቋቋም የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

30

ከሚሴ: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የተገነቡ የመሠረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተሳትፈዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በከሚሴ ከተማ በመልሶ ማቋቋም የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለማኅበራዊ ዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የተገነቡ ፕሮጀክቶችን በማልማት አምራች ዜጋ እንዲፈጠር ለማስቻል በቀጣይ በቅንጅት ሊሠራ ይገባልም ነው ያሉት።

የአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) በክልሉ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው መልሶ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም አሥረድተዋል።

በክልሉ በነበሩ ጦርነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ጠቅሰው መልሶ ለማልማት እና ወደ ሥራ ለማስገባት ጽሕፈት ቤቱ ከክልሉ መንግሥት እና ረጅ ተቋማት ጋር እየሠራ ነው ብለዋል።

በከሚሴ ከተማ በመልሶ ማቋቋም የተገነቡ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው የተገነቡ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል። በቀጣይም የማኅበረሰቡን ችግር በመለየት እንደሚሠራ አብራርተዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመልሶ ማቋቋም በታቀፉ ወረዳዎች ከ1ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲኾኑ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ መንግሥት ጋር በቅንጅት መሠራቱንም ጠቅሰዋል።

በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የከሚሴ ከተማ አሥተባባሪ እስማኤል ናስር በበኩላቸው ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑ ፕሮጀክቶች መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላ፣ ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ይገኙበታል ብለዋል።

በከተማው በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር ሥራ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በከተማው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መታቀዱን ነው የገለጹት።

የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማው በመልሶ ማቋቋም የተገነቡ ፕሮጀክቶች አምራች ዜጋን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። ተገቢውን ጥበቃ ለፕሮጀክቶቹ እንደሚያደርጉም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግቦቻችንን ለማሳካት ሰላም ቁልፍ ጉዳይ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የችሮታ ጉዳይ ሳይኾን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው።