
ባሕር ዳር፡ጥር 28/2011 ዓ.ም(አብመድ)በጀልባ መስመጥ አደጋ የኢትዮጵያውያን ህይወት በማለፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገለፀ፡፡
በጅቡቲ ሰሜን-ምስራቅ አቅጣጫ ኦቦክ በተሰኘች አስተዳደራዊ-ክልል በሚገኘው ጎዶሪያ የተባለ ስፍራ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ የመን ለመሸጋገር ሲሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በጀልባ መስመጥ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ባወጣው የሀዘን መግለጫ አደጋው ጥር 21 ቀን 2011ዓ.ም መድረሱን አስታውቋል። በዚህም ጥልቅ ሃዘኑን ገልጧል፡፡
‹‹በአደጋው የቅርብ ዘመዶቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ጓደኞች ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እመኛለሁ›› ብሏል ሚኒስቴሩ።
በጅቡቲ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር መሐመድ ሐሰን የተመራ 4 አባላት ያሉት የልዑክ ቡድን ከጅቡቲ መንግሥትና ከዓለም-አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበርና የስደተኞች ድርጅት ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
ልዑኩ አደጋው ከተከሰተበት ከኦቦክ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ጎዶሪያ የተባለ ስፍራ በመሄድ በሕይወት የተረፉትን ሰዎች አነጋግሯል ብላል ሚኒስቴሩ፡፡
እስካሁን በተገኘው መረጃ መሰረት በአደጋው የመናዊ ዜግነት ያለው የጀልባው ካፒቴን እና 57 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ሁሉም ጎዶርያ በተሰኘው ስፍራ ቀብራቸው ተፈጽሟል ብሏል ኤፍቢሲ የሃዘን መግለጫውን ጠቅሶ እንደዘገበው፡፡
16 ዜጎች በህይወት መትረፋቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡ ከዓለም-አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበርና ስደተኞች ድርጅት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ህክምናና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ከአደጋው የተረፉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 347 የሚሆኑ ሌሎች ወደ የመን ሊጓዙ የነበሩ ዜጎች የኢትዮጵያ ሚሲዮን የአደጋውን አስከፊነት እንዲገነዘቡ ካደረገ በኋላ ወደ አገራቸው በፈቃደኝነት ለመመለስ ስለወሰኑ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ በፍጥነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ሁለተኛውን ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንም ነው ያስታወቀው፡፡