ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ማስፋት ይገባል።

19

ጎንደር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በክበባት ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉ ስለበሽታው ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረጉን የአዘዞ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተማሪዎች በክበባት ተሠባሥበው መማራቸው ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው እና ለትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ስለበሽታው እንዲያስረዱ ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።

‎የአዘዞ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፀረ ኤድስ እና የሥነተዋልዶ ጤና ክበብ ተጠሪ መምህር ሙሉጌታ ክፍሉ የጤና ባለሙያዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን በመጋበዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለተማሪዎች እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት የተማሪዎች አገልግሎት የነርስ ባለሙያ ሠናይት ኃይለሥላሴ እንደ የክፍል ደረጃቸው ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ክበባትን በማቋቋም እየሠራ መኾኑን ገልጿል።

ወጣቶች ከበሽታው እራሳቸውን እንዲጠብቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በክበባቱ እየተሰጠ መኾኑን በጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ክትትል እና ግምገማ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሲስተር ዘነበወርቅ ንጋቱ አመላክተዋል።

በየትኛውም አጋጣሚ ‎የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ትምህርት መስፋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

‎የበሽታው ስርጭት ያለበትን ደረጃ በመገንዘብ ጥንቃቄ በማድረግ ጤናማ እና አምራች ዜጋ መፍጠር እንደሚገባም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ መልዕክት አስተላልፏል።

ዘጋቢ፦ ተስፋየ ጋሹ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲስ አበባ ሁሉም እጆች ያበጃጇት የኅብረብሔራዊነት እና የልማት ተምሳሌት ናት” አቶ አገኘሁ ተሻገር
Next article“ግቦቻችንን ለማሳካት ሰላም ቁልፍ ጉዳይ ነው” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)