
አዲስ አበባ: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።
በዚህ በዓል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ እና የተዛነፉ አመለካከቶችን መታገል ካልተቻለ የሀገረ መንግሥቱ ግንባታ እንቅፋት ይኾናል ነው ያሉት። ምክክር ወደ ዕውነት የሚያደርስ እና ኅብረብሔራዊ ሀገር ለማጽናትም ጠቃሚ መኾኑን አንስተዋል።
አዲስ አበባ የጋራ ከተማ፣ የሁሉም እጆች ያበጃጇት፣ ኅብረብሔራዊነት ያደመቋት እና የሁሉም ላብ የፈሰሰባት ኅብረብሔራዊ ከተማ ናት ብለዋል።
ይህች ከተማ ልዩ ልማት እና ግንባታ በማከናዎኗ ትልልቅ የዓለም አቀፍ ሥብሠባዎች ማከናወን መቻሏን ጠቅሰዋል።
ከተማዋ የሠራችው ልማትም በከተሞች መካከል ትስስር መፍጠር እና ያም ለኅብረብሔራዊ ሀገር ግንባታ ሥራዎች መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች ባሕል እና ትውፊት ለቱሪዝም ስበት ማዕከል ኾኖ እያገለገለ እንደኾነ አስረድተዋል። በዚህ የጋራ ማንነት ማጉያ የጋራ ቤት በኾነችው አዲስ አበባ ላይ ኅብረብሔራዊነት ጠንካራ አንድነትን ለማጎልበት ለሚሠራ ሥራ መሠረት የሚጥል እንደኾነም ጠቁመዋል።
የጋራ እጣ ፋንታ እና የጋራ ነገ ያለው ሕዝብ በመኾኑ ብልጽግናን ማረጋገጥ፣ እህትማማች እና ወንድማማችነትን ማጠናከር ብሎም መገንባት ለሀገር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
