
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በአማራ ክልል ለሚገኙ ለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት 3 ሺህ መጻሕፍትን ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ታሪኩ በላቸው በክልል ለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት ለሚገኙ ሰዎች እንዲያነብቧቸው የሥነ ልቦና፣ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ የምጣኔ ሀብት እና ፖለቲካ ዘርፎችን ያካተቱ 77 ዓይነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
የመጻሕፍት ድጋፉ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባሕሪ ምክንያት አንድ ቦታ ብቻ ሆነው ለሚያሳልፉ ታካሚዎች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ‘‘በተለያዩ ምክንያቶች ከዚህ በፊት መጻሕፍትን ለማንበብ ጊዜ ላላገኙ በለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት ለሚገኙ ሰዎች ምቹ የአዕምሮ ምግብን ፈጥሮላቸዋል’’ ነው ያት አቶ ታሪኩ፡፡
በክልሉ እስከዛሬ ረፋድ ድረስ ብቻ 185 ሰዎች በለይቶ ሕክምና መሥጫ ማዕከላት በሕክምና ላይ እንደሚገኙ አቶ ታሪኩ አስታውቀዋል፤ ቢሮው መሰል የመጻሕፍት ድጋፍ ለማግኘትና በይነ መረብ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተወካይ አቶ አዘዘ ጌትነት ኤጀንሲው በመላው ሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ 9 ሺህ 500 መጻሕፍትን በየክልሉ ለሚገኙ ታካሚዎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን ‘‘በለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት የሚገኙ ሰዎች በቆይታቸው መጻሕፍትን በማንበብ የሥነ ልቦና ጥንካሬ እንዲያገኙ ያስችላል’’ ብለዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የንባብ ባህልን ማዳበሪያ ሆኖ እንዲያልፍ ኤጀንሲው የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም እየሠራ መሆኑንም አቶ አዘዘ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም አስተባባሪነት በተደረገው ርክክብ ለአማራ ክልል ድጋፍ የተደረጉ መጻሕፍት ግምታቸው 900 ሺህ ብር እንደሚደርስ ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
