
ባሕር ዳር: ኅዳር 2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሴቶች ማኅበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስጀመረውን ተግባራት በተለያዩ አካባቢዎች ርክክብ እያደረገ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አረጋዊ እናት ቤት ገንብቶ አስረክቧል፡፡ ርክክቡ የተካሄደው የማኅበሩ የቦርድ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው፡፡
እማሆይ አያል ዓለሙ በባሕር ዳር ከተማ ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እና የ85 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ አራት ልጆችን ወልደው፣ አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተው የነበረ ቢኾንም ልጆቻቸውን በሞት መነጠቃቸውን ነግረውናል፡፡
በልጆቻቸው ሃዘን የተጎዱት እማሆይ አያል የመኖሪያ ቤት ቢኖራቸውም ቤታቸው በማርጀቱ በክረምት ከላይ ዝናቡ፣ ከታች ጭቃው እና ቅዝቃዜው ሕይዎታቸውን ስቃይ አድርጎባቸው እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ ጧሪ የሌላቸው በመኾኑም ሕይዎታቸው ችግር ላይ እንደነበር ነው የገለጹልን፡
የአማራ ሴቶች ማኅበር ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ቤታቸው ፈርሶ በአዲስ እንዲሠራ አስጀምሮት ነበር፡፡ የተጀመረው ግንባታ ተጠናቅቆ ዛሬ የቤት ዕቃ እና አልባሳት ተጨማሪ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው በመግባታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ላደረጉ አካላትም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከ43 ዓመታት በላይ አብረው በጉርብትና የኖሩት ወይዘሮ ፋጢማ ሁሴን እማሆይ አያል ረዳት የሌላቸው በመኾኑ ቤታቸው አርጅቶ ዝናቡ እና ነፋሱ እየተፈራረቀ ኑሯቸውን ስቃይ አድረጎባቸው ነበር ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ቤታቸው በአዲስ ተገንብቶ በማየታቸው እንደተደሰቱ እና ይህንን ላደረጉ የአማራ ሴቶች ማኅበር ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ እንደዚህ ዓይነት መሰል ችግር ያለባቸውን ሰዎች የማገዝ ተግባሩ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ የዚህ በጎ ተግባር መነሻ ዓላማው በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ወራት ሲሰጥ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ መታሰቡ ነው ብለዋል፡፡
“በመተባበር የማይገፋ ተራራ እና የማይቀረፍ ችግር የለም” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ አቅመ ደካሞችን ማገዝ የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ሕዝብ የቆየ የመተጋገዝ ባሕል አለው፤ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ ድህነትን ለማሸነፍ መሥራት አለብን ብለዋል፡፡

ማኅበሩ በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር ከ800 በላይ ቤቶች በአዲስ ተገንብተው እና ከ1ሺህ 300 በላይ ቤቶች ተጠግነው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል ነው ያሉት፡፡ ከ600 ሺህ በላይ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ጊዜያዊ ድጋፍ እንደተደረገላቸውም አንስተዋል፡፡
እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ማኅበረሰቡን፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን እና ሌሎች አጋር አካላትን በማስተባበር እንደተሠራ ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ ከድጋፍ ባለፈ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ መሠራቱንም አንስተዋል። በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎቻቸው ላይ ስኬታማ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ሴቶች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ዳርእስከዳር ጌቴ ማኅበሩ ጾታን መሠረት ያደረገ ሲኾን የሴቶችን ተጠቃሚነት በበጎ ፈቃድ ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከታቀዱ ሥራዎች መካከል አንዱ የኾነው የዛሬው የቤት ግንባታ ሥራ በባሕር ዳር ከተማ አመራሮች አማካኘነት ችግረኛ ተብለው ተለይተው በተሠጡት መሠረት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ተግባሩ የማኅበሩ አንዱ ዕቅድ ነው፤ ለእማሆይ አያል ሁለት ክፍል ቤት የሚኖሩበት እና ተጨማሪ ሁለት ክፍል የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመኾኑ እያከራዩ እንዲጠቀሙ በማሰብ በጥቅል አራት ክፍል ቤቶች ተገንብቶ ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡
በቤታቸውም አልጋ እና ሶፋ እንዲሁም ተጨማሪ አልባሳትን ጨምሮ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል፡፡ ለዚህም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
አቅመ ደካሞችን እና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለማገዝ በሚደረገው ጥረት ማኅበሩ ተሳትፎውን እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ማኅበሩ ሃብት ስላለው ሳይኾን ማድረግ ይቻላል በሚል አስተባብሮ ሰዎችን ለመርዳት እየሠራ ያለ መኾኑን አንስተው ሁሉም ካለው ላይ ለሌለው በማካፈል መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
