
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሁለት ዓመታት በፊት የግንባታ ሂደቱ ተስተጓጉሎ የነበረው የደብረ ማርቆስ – ደብረ ኤሊያስ – ተምጫ እና ጭምት መገንጠያ – ጭምት ከተማ መንገድ ግንባታ ሂደት ዳግም ተጀምሯል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በ2012 ዓ.ም የተጀመረ ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸም 52 ነጥብ 8 በመቶ ከደረሰ በኋላ በጸጥታ ምክንያት የግንባታ ሂደቱ ተስተጓጉሎ እንደነበር ይታወቃል።
ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ እና ግንባታውን ለማስቀጠል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ከየአካባቢው የጸጥታ መዋቅር እና የመስተዳድር አካላት እንዲሁም ግንባታውን ከሚያከናውነው ፋል ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ እና አማካሪ መሐንዲሱ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችም ተደርገዋል። አሁን ላይ ጥረቱ በመሳካቱም የግንባታ ሂደቱን ማስቀጠል ተችሏል።
እንደ ኢትዮጽያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ የመንገድ ዳር የዲች ሥራ ግንባታዎች እየተሠሩ ሲኾን ግንባታውን በሙሉ አቅም ለማስቀጠል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ተብሏል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 80 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሸፍናል። ለግንባታው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በፌደራል መንግሥት በጀት ተይዞለታል። የማማከር እና የቁጥጥር ሥራውን ኢንጅነር ዘውዴ እስክንድር እና ኩባንያው በማከናወን ላይ ይገኛል።
የመንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ በነባሩ ጠባብ የጠጠር መንገድ ይወስድ የነበረውን የስድስት ሰዓታት ጉዞ ወደ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳጥራልም ተብሏል።
የመንገዱ ግንባታ ምርታማ የኾኑትን የጎዛመን እና የደብረ ኤሊያስ ወረዳዎችን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ነው የተባለው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
