አማራ ባንክ ከታክስ በፊት 655 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።

22

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ባንክ የባለአክሲዮኖች አራተኛ ዓመት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሽ እያካሄደ ነው።

ባንኩ ጠቅላላ ሀብቱ 43 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር) ባንኩ በ2016 እና 2017 ሩብ ዓመት ገብቶበት ከነበረው ችግር በመውጣት ተስፋ ሰጭ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ እና ጤናማ ባንክ በመኾን ጠቅላላ ሃብቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ23 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመላክተዋል።

15 በመቶ የነበረውን ትክክል ያልኾነ የብድር ምጣኔ ወደ 4 በመቶ በታች ማውረድ ተችሏልም ብለዋል።

የተከማቹ የደንበኞች ክፍያዎችን መፈጸም፣ የተከማቸ የውጭ እዳ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን፣ አሁን ላይ በቂ የውጭ ምንዛሬ መኖሩ፣ ከፍተኛ ገንዘብ በማሰባሰብ እና አዲስ የብድር ጥያቄዎችን ማስተናገድ መቻሉንም በአብነት አንስተዋል።

በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

170 ሺህ ባለአክሲዮኖችን ያቀፈው አማራ ባንክ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በማሳደግ ላይ ነውም ተብሏል። ባንኩ በ2017 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 655 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።

በቀጣይ የደንበኞቹን ቁጥር ማስፋት፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ዘርፉን መደገፍ፣ የዲጂታል አማራጮችን ማጠናከር እና በኢንቨስትመንት ባንክ እና በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ለመሠማራት እንደሚሠራም የባንኩ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር ዮሐንስ አያሌው አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ባንኩ በፋይናንስ ዘርፉ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ መጽደቁ ተገልጿል። የፍኖተ ካርታው ርዕይ በ2022 ከአራቱ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ባንኮች አንዱ እንዲሁም በ2032 ደግሞ ከአፍሪካ 40 ቀዳሚ ባንኮቾ አንዱ መኾን እንደኾነም ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
Next articleየኮሪደር ልማት ለጎንደር ከተማ ከውበትም በላይ ችግሮችን የፈታ ነው።