
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 50ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ ነው፡፡ ስትራቴጂው ለዜጎች አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ እና መሠረተ ልማቶቹን ለማስፋፋት፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በተሻለ መንገድ ማሳካትን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ምክር ቤቱም በስትራቴጂው ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር በተፈረሙ ሁለት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዘላቂ እና ንፁህ የኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 294 ሚሊየን 900 ሺህ ኤስ. ዲ. አር የብድር ስምምነት ሲሆን የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጠናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ 20 ሚሊየን ኤስ. ዲ. አር የብድር ስምምነት ሲሆን የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ31 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ሁለቱም ብድሮች ከወለድ ነጻ እና 0 ነጥብ 75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡ ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቶቹ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ መኾናቸውን በማረጋገጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።
3. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍዎችን ለመወሰን በቀረቡ ሁለት ረቂቅ ደንቦች ላይ ነው፡፡ ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት የሚያወጡትን ወጪ ሸፍነው ገቢያቸውን በማሳደግ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ በማስፈለጉ የተገልጋዩን አቅም ባገናዘበ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው በአራት የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ሌሎቹ ሁለት ስምምነቶች ከሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ፍርደኞችን ለማስተላለፍ የተደረጉ ናቸው፡፡ ሌላው ከደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር የተደረገው የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ነው፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቶች ቢጸድቁ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ውጤታማ የወንጀል መከላከል የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር የሚያስችላት መኾኑን በመገንዘብ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010ን ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ስርዓቶችን በአዋጁ እና በተሻሻለው የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1358/2017 መሰረት ግልፅ እና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ለመተግበር እንዲያስችል ሆኖ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 114/1997 ለማሻሻል በቀረበ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
