ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል።

7

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የምርት ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የሕገ ወጥ እና ጸረ ኮንትሮባንድ ጥምር ግብረ ኃይል የወንጀል ጉዳይ ቴክኒክ ኮሚቴ የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።

በግምገማው የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በአማራ ክልል የገበያ ሥርዓቱ ከሕገ ወጥነት ነጻ ኾኖ እንዲመራ ለማድረግ የሚደግፉ፣ የሚቆጣጠሩ እና የሚያስተካክሉ ተግባራትን የሚሠሩ ተቋማት በትብብር የመሥራታቸውን አስፈላጊነት አንስተዋል።

የንግድ ሥርዓቱ በሕገ ወጦች ተጠልፎ ሕጋዊ ነጋዴዎች ከንግድ ሥርዓቱ እንዳይወጡ፣ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት፣ የመንግሥት ገቢ እንዳይቀንስ፣ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም እና በአጠቃላይ የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እንዳይሸረሸር የገበያ ሥርዓቱን ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ነጻ የማድረግን አስፈላጊነትም ገልጸዋል።

ሕጋዊ የገበያ ሥርዓትን ለማጠናከርም የወንጀል ጉዳዮች ክትትል የቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራዎችን ሲፈጽም መቆየቱን ነው የተናገሩት። የግንዛቤ ፈጠራ፣ በሕገ ወጦች ላይ እርምጃ መውሰድ እና ሕገ ወጥ ንብረትን የመውረስ ሥራ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።

ዘርፉ ለሕገ ወጦች ያለው ተጋላጭነት ሰፊ መኾኑን ያነሱት አቶ ብርሃኑ ችግሩን በአንድ ጊዜ መቅረፍ እንደማይቻል ገልጸዋል። በቀጣይም ጥብቅ ክትትል እና ተቆራርጦ መሥራት እንደሚፈልግም አንስተዋል።

የሩብ ዓመቱ ሥራዎችን ገምግሞ በማጠናከር እና ክፍተቶችንም በማረም የዘርፉን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ዘላቂ ለማድረግ የኮሚቴው ተነሳሽነት አስፈላጊ እንደኾነ ነው የገለጹት።

የውይይቱ ዓላማ ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል እና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን በማጠናከር ምጣኔ ሃብቱን ከጥቃት መከላከል መኾኑን ተናግረዋል። የግብረ ኃይሉ ተዋናዮችም ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን በሚደረገው ርብርብ በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

በውይይቱ፦

👉 ግብረ ኃይሉ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል፤

👉 ተንቀሳቃሽ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ፈጣን የሕግ ቅጣት ለማሰጠት ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣

👉 በሕገ ወጥ ኬላዎች የሚሰበሰበው ክፍያ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ በሸማቹ ላይ ጫና እየፈጠረ ስለኾነ መስተካከል እንዳለበት፤

👉 በድንበሮች ሕገ ወጥ የሸቀጦች እና የቁም እንስሳት ወደ ውጭ መውጣት ስላለ በትኩረት ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት፤

👉 የፌዴራል ተቋማት ተደራሽነት አነስተኛ በመኾን በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚታይ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመግታት በድንበሩ አካባቢ የፍትሕ አካላት የሚመደቡበት ሁኔታ እንዲኖር፤

👉 ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ወደ ሕግ አቅርቦ የማስቀጣት አቅምን መጨመር እንደሚገባ፤

👉 ሕገ ወጥ ንግድ የሚበዛባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ልዩ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ቢቻል፤

ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ተንቀሳቃሽ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለሕግ የማቅረብ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም ተነስቷል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትኩረት የሚያሻው የስኳር በሽታ”
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።