“ትኩረት የሚያሻው የስኳር በሽታ”

4

ፍኖተ ሰላም: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስኳር በሽታ በደም ውሰጥ የተዛባ የደም መጠን መኖር ማለት ነው። ይህ የሚኾነው ሰውነታችን በደም ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን በአግባቡ መቆጣጠር በማይችልበት ጊዜ ነው።

ይህም በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ እንዲል ስለሚያደርግ ከፍተኛ የጤና መታወክ ያስከትላል።

ህመሙ የሚከሰተው ሰውነት በደም ስር ውስጥ ያለን ስኳር ወይንም ግሉኮስ በሙሉ በተገቢው መጠን ማመንጨት ሲያቅተው ነው።

የዓለም የስኳር በሽታ ፌዴሬሽን በቅርቡ ይዞት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ 589 ሚሊዮን ሰዎች የስኳር በሽታ አለባቸው።

በኢትዮጵያ ደግሞ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር በሽታ ታማሚዎች ናቸው ይላል መረጃው።

አቶ ኃይሉ መከተ የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ የስኳር ታማሚ ኾነው በፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ ነው ያገኘናቸው።

ከአምስት ዓመት በፊት ከዕለታት በአንድ ቀን መደበኛ ሥራቸውን እየከወኑ ሳለ አዙሯቸው እንደወደቁ ይናገራሉ። ከዚያም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ሲያደርጉ የስኳር በሽታ እንደተገኘባቸው ትውስታቸውን አጫውተውናል።

በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ይሠሩት የነበረውን መደበኛ ሥራ እና ሌሎች ተግባራትን እንደፈለጉ ለማስቀጠል እንደተቸገሩ ገልጸውልናል። አሁን የህክምና ክትትል በማድረግ እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ በማድረግ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ሌላው ከጅጋ ከተማ ወደዚሁ ሆስፒታል ለስኳር ህመም ክትትል ሊያደርጉ መጥተው ያገኘናቸው አቶ ፍሬው በላይ ደግሞ ለሌላ ህክምና ወደ ጤና ተቋም ሄደው ህመሙ እንደተገኘባቸው ገልጸውልናል።

በጤና ተቋም በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ህመሙን ለመግታት አመጋገባቸውን ለማስተካከል እንደተገደዱም አጫውተውናል። በሽታው ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ፈታኝ ስለኾነ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም አውስተዋል።

በፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል የቤተሰብ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር አማረ ወዳጀ አይነት አንድ፣ አይነት ሁለት እና ሌሎች የስኳር በሽታ ስለመኖራቸው ገልጸዋል።

ስለአይነት አንድ የስኳር ህመም ምልክቶች ሲያብራሩ ውኃ ቶሎ ቶሎ መጠማት፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት መሽናት፣ የዓይን ዕይታ መቀነስ እና ተከታታይነት ያለው የድካም ስሜት ከምልክቶቹ ውስጥ እንደኾነ ተናግረዋል። ይህ በሽታ በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉትን የሚያጠቃ መኾኑንም ገልጸዋል።

አይነት ሁለት የስኳር ህመም ግን ምንም ምልክት ሳያሳይ ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ ተደብቆ ሊቆይ እንደሚችል አስረድተዋል። አብዛኛው የስኳር ህመምተኞችም የአይነት ሁለት ተማሚዎች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

ከአጠቃላይ የስኳር ህመምተኞች ውስጥም 95 በመቶ የሚኾኑት የአይነት ሁለት ታማሚዎች መኾናቸውን የዓለም የስኳር ፌዴሬሽን መረጃ ያሳያል። ብዙውን ጊዜ በሽታው በህመምተኞች ላይ መኖሩ የሚረጋገጠው ለሌላ ህክምና ወደ ጤና ተቋም ሲመጡ እንደኾነም ገልጸዋል።

ዶክተር አማረ በስኳር በሽታ የተያዘ ሰው አስፈላጊ ጥንቃቄ እና ክትትል ካልተደረገ ለከፋ ችግር እና ለሌሎች በሽታዎች ጭምር ሊያጋልጥ እንደሚችል ተናግረዋል።

በዚህም የደም ስር መጎዳት፣ ለልብ ድካም፣ ለኩላሊት በሽታ፣ ዕይታ ማሳጣት፣ እግር ላይ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ኢንፌክሽን እና ሌሎች ጉዳቶችን ብሎም እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ነው የገለጹት።

ከበሽታው ራስን ለመከላከል የኑሮ ዘይቤን ማስተካከል ዋነኛው መፍትሔ መኾኑንም ይመክራሉ። በተለይ አትክልት እና ፍራፍሬ መመገብ፣ ቅባት እና ጨው ከሚበዛባቸው ምግቦች እና መጠጦችን ከመጠቀም መታቀብ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ከመጠን በላይ የኾነ የሰውነት ውፍረትን መቀነስ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር ዋናው መፍትሔ ነው ይላሉ።

ብዙውን ጊዜ ለስኳር ህመም ምርመራ ብሎ ወደ ጤና ተቋም የሚመጣ ታካሚ አለመኖሩን የሚገልጹት ዶክተር አማረ ይህም ለበሽታው ትኩረት አለመሰጠቱን ይጠቁማል ነው ያሉት።

በሽታው አስከፊ እና እስከ ሞት የሚያደርስ በመኾኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በመመርመር እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ምክረ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የሚወጡ አዋጆች እና ሕጎች ተፈጻሚ ሊኾኑ ይገባል።
Next articleሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል።