ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የሚወጡ አዋጆች እና ሕጎች ተፈጻሚ ሊኾኑ ይገባል።

6

ደብረ ታቦር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ እና በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ” አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት ነው ዞናዊ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የተካሄደው።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳተኞች ምክር ቤት ቴክኒሻል ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ሀብቴ ዓለምነው (ዶ.ር) የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ ቀን ክብረ በዓል ብቻ ሳይኾን የሁልጊዜ ተግባራችን ነው ብለዋል። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና አሳታፊ ሥራዎች ስለመተግበራቸውም አውስተዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አካል ጉዳተኞች እና ማኅበራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሰሐ ኃይሌ የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ በኖረበት የሕይዎት ጎዳና ሁሉ አካል ጉዳተኝነት የተከሰተ፣ አሁንም ያለ እና ወደፊትም የሚኖር ሁለንተናዊ ገጠመኝ ነው ብለዋል።

ቁጥሮች እንደሚያሳዩት እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 2022 በዓለም ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ እና በኢትዮጵያ ደግሞ 17 ነጥብ 6 በመቶ የአካል ጉዳተኛ ምጣኔ እንዳለ ያሳያል ነው ያሉት። አሁን ላይ በዓለማችን እና በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ካስገባን ደግሞ ቁጥሩ በጣም አስጊ ደረጃ ላይ እንደሚኾንም አመላክተዋል።

የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር ዋና ዓላማው አካል ጉዳተኞች የእኩል ዕድል እና ተሳትፎን በማረጋገጥ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማስቻል እንደኾነ ነው የተናገሩት። ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም የተሳሳተ አመለካከትን መቅረፍም ሌላው ዓላማ ነው ብለዋል። ቀኑን ስናከብር ወደፊት ሰለምንሠራቸው ሥራዎች እያሰብን አካታች ተግባራትን እናከናውናለን ነው ያሉት።

“ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የሚወጡ አዋጆች እና ሕጎች ተፈጻሚ ሊኾኑ ይገባል” ያሉት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር የሴቶች፤ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ተወካይ ኀላፊ መላሽ ክንዴ ናቸው።

አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ጉዳዮች መብቶቻቸው መጠበቅ እንደሚገባው አንስተዋል። አካለ ጉዳተኞች አዋጆችን ማወቅ እና መብታቸውን ለማስከበር ግንዛቤ ሊይዙ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካትቶ ትግበራ ሥራ አሥፈጻሚ ንግሥቴ ፍሰሐ በዩኒቨርሲቲው 60 የሚኾኑ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በዓሉን አብረን ስናከብር እንቁ ተማሪዎቻችን በማብቃት እና በማሳተፍ ነው ብለዋል።

አካል ጉዳት መቸም ሊፈጠር የሚችል ነው። ይህንንም በመረዳት አመለካከት እና ግንዛቤ የምንፈጥርበት በዓል እንደኾነ ነው የገለጹት። ለተማሪዎቻችን ምቹ የመማሪያ ቁሳቁስ እና ግብዓት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ለተጠቃሚነታቸው እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።

የውይይቱ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች የመማሪያ ክፍሎች፣ መጸዳጃ ቤቶች እና አስፈላጊ ቁሳቁሶች በተሻለ ደረጃ እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምስራቅ ዕዝ ከሕዝብ የተዘረፈን 649 ኩንታል እህል በቁጥጥር ስር አዋለ።
Next article“ትኩረት የሚያሻው የስኳር በሽታ”