የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ ምርመራ ጀመረ፡፡

346

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥበብ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መካከልና መቆጣጠር ግብረ ኃይል ስብሳቢ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ማዕከሉ ለሆስፒታሉ ተገልጋዮችና ለባሕር ዳር ከተማ በስፋት ከማገለገል ባለፈ የክልሉን የምርመራ አቅም በማሳደግ ረገድ ድርሻው የጎላ እንደሚሆን ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው ክልሉ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚ መሆኑን በመግለጽም ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶክተር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አሁን ምርመራ የጀመረው ማዕከል ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ለጥናትና ምርምር እገዛ እንዲያደርግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ የሺጌታ ገላው (ፕሮፌሰር) ለአብመድ እንዳሉት ጥበብ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀን 96 ናሙናዎችን መርመር የሚያስችል ላቦራቶሪ ሥራ ጀምሯል፡፡ በሆስፒታሉ አንድ የመመርመሪያ ማሽን እንዳለና ወደፊት ተጨማሪ ለማምጣት እንቅስቃሴ እንደተጀመረም አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ ዳይሬክተር ማንአምኖት አገኝ እንደተናገሩት የጥበበ ግዮን ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ በክልሉ ስድስተኛው የናሙና መመርመሪያ ሆኗል፡፡ የክልሉን የምርመራ አቅም ከፍ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ወልዲያ ላይ ምርመራ በቅርብ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡ በክልሉ በቀን እስከ 1 ሺህ 500 ናሙናዎችን ለመርመር እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ማንአምኖት “መተማ ላይ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ብለዋል፤ ነገር ግን ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የቻይና አፍሪካ ትብብር የማይተካ ሚና እንደሚኖረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ፡፡
Next articleበለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት ለሚገኙ ሰዎች መጻሕፍት ተበረከተላቸው።