
ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር በመጣመር ባካሄዱት የተጠና ኦፕሬሽን ጽንፈኛው ቡድን ከሕዝቡ የዘረፈውን 649 ኩንታል እህል በቁጥጥር ስር መዋሉን የጃቢጠህናን ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በተካሄደው ኦፕሬሽን ከሞት እና የአካል ጉዳት የተረፈው ጽንፈኛ ከሕዝብ በመዝረፍ ለስንቅ ሲጠቀምበት የቆየውን ቁሳቁስ ጥሎ መሸሹ ተመልክቷል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይችላል አድማሱ ቡድኑ ለሕዝብ እታገላለሁ ቢልም ተግባሩ የሚያሳየው ግን ዝርፊያ እና ግድያ መኾኑን ጠቁመዋል።
በኦፕሬሽኑ በጃቢ ጠህናን ወረዳ ውብሸት ቀበሌ ከ242 ኩንታል በላይ፣ በጉየ ቀበሌ 200 ኩንታል፡ በጉለም ቀበሌ 150 ኩንታል እና በሌሎች ቦታዎች 57 ኩንታል ያከማቸውን እህል በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
ከብር ሸለቆ የእርሻ ልማት፣ ከባለሃብቶች እና ከአርሶ አደሩ የዘረፈው እህል ተከማችቶ መገኘቱንም ኀላፊው አስረድተዋል።
ማኅበረሰቡን ለእናንተ ነው የምንታገለው፣ ነጻ ልናወጣችሁ ነው እያለ በሃሰት ትርክት እያጭበረበረ በዘረፋ የራሱን ጥቅም በማግበስበስ ላይ እንደሚገኝ የሰሞኑ ኦፕሬሽን ያስገኘው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።፡
አሁን ላይ የወረዳው ሕዝብ ከዚህ ዘራፊ ቡድን ለመገላገል ከመከላከያ ሰራዊት እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጎን በመሰለፉ ኦፕሬሽኑ የተሳካ እንዲኾን አስችሏል ብለዋል።
ጽንፈኛ ቡድን ከፀጥታ ኀይላችን ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ሰርጎ በመግባት የእርድ እንስሳትን በመዝረፍ፣ ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት ማድረሱንም ተናግረዋል።
ዘራፊ ቡድኑ ተማሪዎች እንዳይማሩ እና ህሙማን ወደ ጤና ተቋም ሄደው እንዳይታከሙ በራሱ ወገን ላይ በፈጸመው በደል ከሕዝብ እንዲነጠል አድርጎታል ነው ያሉት።
ቡድኑ በፈጸመው ድርጊት ከሕዝብ መነጠሉን በሰሞኑ ኦፕሬሽን ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት አቶ ይችላል ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
አርሶ አደሩ ያመረተውን በመቀማት ለርሀብ እየዳረገው ካለው ቡድን ለመገላገል ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከክልሉ ጸጥታ ጎን በመሰለፍ ሰላሙን ማረጋገጡ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
