
ጎንደር: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አካል ጉዳተኞችን ከተረጅነት በማላቀቅ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን መጨመር እንደሚገባ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት የአካል ጉዳተኞች ቀን እንደሚከበር ገልጿል።
መምሪያው በዓለም ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞችን ቀን ምክንያት በማድረግ የከተማው ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የፓናል ውይይት መነሻ ጹሑፍ በመርሐ ግብሩ የቀረበ ነው። በዓለማችን 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ እና በጎንደር ከተማ ደግሞ ከ85ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች መኖራቸው ተጠቅሷል።
በዓሉን ማክበር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ኹኔታዎችን ለመፍጠር፣ የአመለካከት ክፍተቶች ላይ ግንዛቤን ለማዳበር እና ትብብር ብሎም ቅንጅትን ለማሳደግ አስፈላጊ መኾኑን የጎንደር ከተማ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጓዴ ደመቀ አስረድተዋል።
የመንግሥት ተቋማት አካታች በኾነ መንገድ ሥራዎችን ውጤታማ በኾነ መልኩ መምራት ከቻሉ አካል ጉዳተኞች መሥራት እና መለወጥ እንደሚችሉ ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ አወቀ ተፈራ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የመሠረተ ልማት በማሟላት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አካል ጉዳተኞችን ከተረጅነት ማላቀቅ፣ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን መጨመር እና መሠረተ ልማቶች ሢሠሩ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መኾን እንዳለበትም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ማርታ አዱኛ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
