የቋንቋ እና የባሕል ብዝኃነት ለሀገራችን ውበት እና መገለጫዎች ናቸው።

25
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 2ዐኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅምብቢት ወረዳ እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ በጋራ ተከብሯል።
በዕለቱ የበዓሉ ተሳታፊዎች ዲሞክራሲያዊ በኾኑ የተግባቦት መንገዶች የቆዩ ባሕል እና እሴቶቻችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በማናቸውም አጋጣሚዎች በጠበቀ ግንኙነት እና ሰላማዊ በኾነ መንገድ የኖሩ መኾኑንም በዕለቱ አስገንዝበዋል። ይሄንን ነባር እና የቆየ የሁለቱን ሕዝቦች መስተጋብር አጠናክረን እናስቀጥላለን ብለዋል ከሁለቱም ወረዳዎች የመጡ ተሳታፊዎች።
የአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ ገነት ይገዙ የሁለቱ ወረዳ ሕዝቦች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ጠንካራ ትስስር ያላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
የቋንቋ እና የባሕል ብዝኃነት ለሀገራችን ውበት እና የመገለጫዎቻችን ናቸው። ዕድሎችም ናቸው ነው ያሉት። ይሄን ብዝኀነት ዕድል አድርጎ የመቁጠር የረጅም ጊዜ ማኅበረሰባዊ ልምድ የበለጠ ማጎልበት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የቅምብቢት ወረዳ ዋና አፈ ጉባዔ አስታጥቄ ገመቹ አንድነታችንን የሚያስጠብቁ የአብሮነት መንገዶችን በመከተል የሁለቱን አካባቢ ነዋሪዎች ሰላማዊ ግንኙነት ማስቀጠል ችለናል ብለዋል።
ሀገራችን የምትፈልገውን የዲሞክራሲ እና የልማት መንገድ ዳር ለማድረስም ጽንፍ ከወጡ አስተሳሰቦች መውጣት እና መታገል ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
በዓሉ ባለፈው ዓመት በአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ የሁለቱ ክልል ነዋሪዎች በጋራ አክብረው እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት ደግሞ በቅምብቢት ወረዳ መከበሩ ለሰላም፣ ለልማት እና ለዲምክራሲ በጋራ የሰጡትን ትኩረት ማሳያ እንደኾነ አፈ ጉባዔዎቹ ጠቅሰዋል።
በበዓሉ ላይ ተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎች ተገኝተዋል።
በዓሉ በወረዳው ዳሎታ ሱኪ ቀበሌ የሁለቱ ወረዳ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ”ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው።
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቅረፍ ያስችላል።
Next article“የኢኮኖሚ ድርጅቶች መረጃ ስብሰባ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ደረጃ ለማወቅ የሚደረግ እንጂ ሌላ አላማ የለውም” የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት