
አዲስ አበባ: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚከበረውን 33ኛውን የአካል ጉዳተኞች ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
“አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ኅዳር 24/2018 ዓ.ም ይከበራል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ በዓሉ የሚከበረው በአካል ጉዳተኞች ላይ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቅረፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለመስጠት እንደኾነ ገልጸዋል።
መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት እና ሌሎች አካላት በቅንጅት ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠያቂነት በጋራ የሚሠሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።
በዓሉ አካል ጉዳተኞች “እኛ እንችላለን” በሚል መልዕክት በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎች መርሐ ግብሮች እንዲያከብሩት ይደረጋል ነው ያሉት።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዓሉ አካል ጉዳተኞችን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች ምቹ የመሠረተ ልማት፣ የአገልግሎት ዘርፍ እና ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ በመኾናቸው የሚሠሩ የልማት ሥራዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ እንዲኾኑ የክትትል ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
