
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው አራተኛው ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ 49 የአፍሪካ ሀገራት እና አራት ታዛቢ ሀገራት እየተሳተፉ ነው።
በአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ
“ሕገ መንግሥታዊነት እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ያለውን ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየምን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከፍተውታል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ኢትዮጵያ ለሕገ መንግሥታዊ ጉዞ ድርሻ ያበረከቱ ባሕላዊ እና ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት ናት ብለዋል። በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ልምድ እንዳላትም ተናግረዋል።
ሕገ መንግሥቶች በዜጎች መካከል መተማመንን እንዲያጎናጽፉ በሕገ መንግሥት እና የሕግ የበላይት ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ገለልተኛ ዳኝነትን ማጎልበት እና የሥልጣን ክፍፍልን ማስከበር ላይ በትኩረት መሥራ ይገባል ብለዋል።
የሕግ የበላይነት ማስከበር የዜጎችን መብት የሚያስከብር መኾኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ሕገ መንግሥታዊነት እና ውጤታማ የመንግሥት ግንባታ የሚኖረው በፍትሕ እና የሕግ የበላይነት ነው ብለዋል።
እነዚህን ተግባራት እውን ማድረግ ከተቻለ የአፍሪካን 2063 አጀንዳ ማሳካት ይቻላል ነው ያሉት። ሰላም እና ብልጽግናንም ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን እንደምታካፍል እና በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመላክቷል።
የአባል ሀገራቱ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሠሩ የዘርፉ ምሁራን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ልምድ እና ተሞክሯቸውን እንደሚለዋወጡበትም ተጠቁሟል።
ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ በአዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
