ጣና ነሽ ቁጥር ፪ ለተጓዦች ምቾት የምትፈጥር ናት።

24
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጣና ነሽ ቁጥር ፪ ጀልባን ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ መንገደኞችን አሳፍራ ወደ ደልጊ በማቅናት መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምራለች።
በኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሙላት ጸጋ ጣና ነሽ ቁጥር ፪ ለጎብኝዎች እና ለመደበኛ ተጓዦች ሁለገብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሯን አስታውቀዋል።
ጀልባዋ ዛሬ የመጀመሪያውን ጉዞ ከባሕር ዳር ወደ ደልጊ አድርጋለች ብለዋል። በዘመናዊነቷ፣ በፍጥነቷ፣ እና በተሟሉላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚዎች ምቹ መኾኗንም ጠቁመዋል። ይህም በፊት ከነበሩት ጀልባዎች የተለየ እንደሚያደርጋት እና የባሕር ትራንስፖርት ዘርፋንም ከፍ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
አቶ ሙላት እንደገለጹት ጀልባዋ ሦሥት ክፍሎች አሏት። በእያንዳንዱ ክፍል ኤሲ፣ ቴሌቪዥን እና ሌሎችም ግብዓቶች ተገጥሞለታል። ይህም ተጓዦች በአውሮፕላን የመሄድ ያክልን ምቾት የምትፈጥር ናት ብለዋል።
ሐይቁን እያየ ለመጓዝ የሚያስችል ደረጃቸውን የጠበቁ ወንበሮች ተገጥመውላታል። የቪ አይ ፒን ጨምሮ በአንድ ጊዜ እስከ 200 ሰው የማሳፈር አቅም አላት።
ሌሎች ጀልባዎች ከባሕር ዳር ተነስተው ጎርጎራ ለመድረስ እስከ 6፡00 ይፈጅባቸው እንደነበር ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ጣና ነሽ ቁጥር ፪ ግን 3፡00 ብቻ የሚፈጅባት መኾኑን ገልጸዋል። ይህም ከባሕር ዳር ጎርጎራ የደርሶ መልስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።
ጎብኝዎች በምቾት እና በፍጥነት ወደ ሚፈልጉበት መዳረሻ ተጉዘው እንዲጎበኙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራትም ገልጸዋል። ይህም የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና ከፍ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመላክተዋል።
ጀልባዋ ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል አገልግሎት የምትሰጥ መኾኗንም ጠቁመዋል። ጎብኝዎች በማንኛውም ጊዜ በመምጣት በጀልባዋ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየደብረ ማርቆስ ከተማን ገጽታ የሚቀይሩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next article“ኢትዮጵያ ለሕገ መንግሥታዊ ጉዞ ድርሻ ያበረከቱ ባሕላዊ እና ታሪካዊ እሴቶች ባለቤት ናት” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አዲስ አበባ: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።