
ደብረማርቆስ: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት ከአምስት ዓመቱ የአሻጋሪ የዕድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ የተቀዱ ዕቅዶችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ኅብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የከተማውን ገጽታ የሚቀይሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በከተማ ልማት፣ በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ የልማት ዘርፎች ላይ ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድን የማጠናቀቅ እና ባለፈው ዓመት የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን የማስቀጠል ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ የመልሶ ማልማት ተግባራት በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጣቸው የልማት ዘርፎች ናቸው ነው ያሉት፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ ለሌማት ትሩፋት እና ለከተማ ግብርና ዘርፎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የእንስሳት ማድለብ፣ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታ እና የንብ ማነብ ተግባራት በኩታገጠም ታቅፈው ዜጎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በበጀት ዓመቱ ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
በከተማዋ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት የገጠር ቀበሌዎች ግብርናውን በማዘመን ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎችን እና ሜካናይዜሽንን የማስፋት ሥራዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለቀጣይ የተግባር ምዕራፎች አቅም የሚኾኑ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበር አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
