
ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለእጩ ዐቃብያነ ሕግ በፍትሐብሔር እና በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን ተግባር ለማሳወቅ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እና ተቋማዊ ተአማኒነት ለመፍጠር ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።
አሚኮ ያነጋገራቸው እጩ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ ሀብታም ሙሉዓለም ላለፉት ስምንት ወራት በዐቃቤ ሕግ ሙያ በሥልጠና ላይ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በሥልጠናው በንድፈ ሃሳብ እና በፍትሕ ተቋማት ላይ የተግባር ልምምድ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
የአሁኑ ሥልጠና ደግሞ በተግባር ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ተግዳሮቶች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚያመላክት ነው ብለዋል።
አሠልጣኞች በሥራ ላይ ያላቸውን ተሞክሮ ያጋሩበት በመኾኑ ለቀጣይ ሥራቸው ትልቅ ስንቅ እንደሚኾንም ተናግረዋል።
እጩ ዐቃቤ ሕግ ዘውዱ ጥጋቡ በሥልጠናው የተገኘው ዕውቀት ክህሎትን የሚያዳብር መኾኑን ነው የገለጹት። ቀደም ብሎ የንድፈ ሃሳብ፣ የተግባር እና የሥነ ምግባር ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውንም አብራርተዋል።
እጩ ዐቃቤ ሕግ ማንደፍሮ ይርሳው በበኩላቸው በሥልጠናው ሕግ በተግባር ሲተረጎም ምን ይመስላል የሚለውን ያዩበት እንደኾነ ገልጸዋል። የነበረውን ብዥታ ያጠራ ነውም ብለዋል።
በሥልጠናው ተቋሙን እዲያውቁ፣ በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸውን ያዩበት መኾኑን ገልጸዋል።
የዐቃቤ ሕግ ሥራ በአብዛኛው የሕዝብን ጥቅም የሚወክል በመኾኑ በቁርጠኝነት ወደ ሥራ ለመግባት እና ኀላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የዐቃቤ ሕግ ሚናው ሠፊ በመኾኑ ሚናቸውን ለመወጣት ጠንክረው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የሕግ ዕውቀት ብቻውን በቂ አይደለም፤ የዐቃቢ ሕግ ሥራ ከተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሠራ በመኾኑ ይህንን ለማወቅ ሥልጠናው አግዞናል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ሥልጠናው ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ መኾኑን ተናግረዋል። ለዐቃቤ ሕግ የሙያ ሥነ ምግባር ፋይዳው ትልቅ ነውም ብለዋል።
ሙያውን ማክበር እና የሙያ ኀላፊነትን ሰብዓዊ በኾነ መንገድ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።በሥልጠናው በሙያው ላይ ለረጅም ጊዜ ከሠሩ ባለሙያዎች ልምድ እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕጎች በወንጀል እና በፍትሐብሔር ሊያውቁ የሚገባቸውን ሕጎች ጠንቅቀው እንዲያውቁ ተደርጓል ነው ያሉት።
የሕዝብ ተቋማትን እና የሕዝብን ጥቅም ወክለው በሚቆሙበት ጊዜ በተግባር ሊገጥማቸው የሚችልን ችግር ቀድመው አውቀው እንዴት እንደሚፈቱት እንዲረዱት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ክልሉ በጸጥታ ችግር ውስጥ በመኾኑ ለዐቃቤ ሕግ ባለሙያዎች የሚገጥሙ ችግሮች ብዙ ናቸው፤ ዐቃቤ ሕግ ማለት ደግሞ ለሕግ እና ለፍትሕ የቆመ በመኾኑ ሙያቸውን ሥነ ምግባር በተላበሰ መንገድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ስንቅ ለመሥጠት የተሰጠ ሥልጠና መኾኑንም ገልጸዋል።
ከያዙት የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት በተጨማሪ የተቋሙን ስትራቴጅክ ዕቅድ እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል።
የዐቃቢ ሕግ ሙያ ሰብዓዊ መብትን ማክበር እና ማስከበርን ጨምሮ ብዙ አገልግሎቶችን ይሰጣል ነው ያሉት። ስለዚህ ሚዛናዊ ኾነው የተጎጅንም የተጠርጣሪንም መብት ባከበረ እና ሕጉ በሚያዘው መንገድ እንዲሠሩ ይጠበቃል ብለዋል።
ሥልጠና በልዩ ሁኔታ የተቋሙ የተግባር አካል ኾኖ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፤ በቀጣይም አዳዲስ ሕጎችን የማስተዋወቅ እና በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ታሳቢ ያደረጉ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
