
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ መልዕክት ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በሥልጠናው የተሳተፉ መሪዎች የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመግታት እየተሠራ ነው ብለዋል። የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል ችግሩን በሚያባብሱ አካላት ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ ዋጋን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የድንኳን ገበያዎችን እያዘጋጁ አማራጮች በቀጥታ ለሸማቾች እንዲያደርሱ እየተደረገ ነው ብለዋል። በገበያዎቹ አማራጮችም የንግድ ሰንሰለቱ ባጠረ መንገድ ለሕዝብ ያቀርባሉ ነው ያሉት።
ሸዶችን በመገንባት ፋብሪካዎች አና ጅምላ ነጋዴዎች ለማኅበረሰቡ ምርት እንዲያቀርቡ እያደረግን ነው ብለዋል። ይህም አምራች እና ሸማችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገናኙ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ገበያን ማረጋጋት የሚያስችል የገበያ ማዕከል እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል። የንግድ ሰንሰለትን ማሳጠር እና ከደላላ ነጻ ማድረግ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ሲያይ ዝም ማለት የለበትም፤ መታገል እና ለመንግሥት አካል ማመልከት አለበት ነው ያሉት። የሕገ ወጥ ንግድ ተባባሪ መኾን እንደማይገባውም አመላክተዋል። ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ከሠራ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር ይቻላል ነው ያሉት።
በደቡብ ወሎ ዞን የጊንባ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ደስታ መኮንን በሕዝቡ ላይ የኑሮ ውድነት ጫና እንዲፈጠር ያደረገው የሰላም አለመኖር ነው ብለዋል። በእኛ አካባቢ ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በቂ ምርት አለ ያሉት ኀላፊዋ የጸጥታው ችግር ግን ምርት እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት።
የምርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል። ሰላም ከተረጋገጠ ኅብረተሰቡ ተንቀሳቅሶ መሥራት ይችላል፣ ምርትም ይንቀሳቀሳል፤ የኑሮ ውድነትም ይቀንሳል ብለዋል።
አንዳንድ ነጋዴዎች እና ደላላዎች የሰላም ችግሩን እንደምቹ አጋጣሚ ይጠቀሙበታል ያሉት ኀላፊዋ እነዚህን አካላት በጋራ መታገል እና መቆጣጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሰላም እንዲረጋገጥ መሥራት እና በሕገ ወጦች ላይ እርምጃ መውሰድ ከተቻለ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አሳቤ አዳነ የኑሮ ውድነትን እያባባሰው የመጣው የሰላም እጦት ነው ብለዋል። ሰላም ሲኖር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይኖራል፤ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ደግሞ ምርትን ተንቀሳቅሶ መሸመት ይቻላል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ጉዳይ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ አካላትንም መታገል እና ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ የተመረተውን ምርት በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ማንቀሳቀስ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ነው ያሉት።
የንግድ ሥርዓቱን ጤናማ ማድረግ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
