
ፍኖተሰላም: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ወቅታዊ የሰላም እና የልማት ተግባራትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የታቀዱ የሰላም እና የልማት ተግባራትን በተሻለ ለማከናወን የገቢ አሠባሠቡ ላይ ትኩረት መሰጠቱን በማብራሪያቸው አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ ታቅዶ እስካሁን 769 ሚሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡንም ገልጸዋል።
የጸጥታ ሁኔታው ከባለፉት የግጭት ዓመታት እየተረጋጋ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለዚህም ኅብረተሰቡ ለሰላም ባለቤት መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ወራት በግብርና ሥራው ላይ ሰፊ ርብርብ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ከብክነት ለመከላከል የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
በዞኑ ላለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እና ለኅብረተሰቡ ተግዳሮት የነበረውን የመብራት ኀይል ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስረድተዋል። በዚህም በፍኖተሰላም ከተማ ያለውን የመብራት ኀይል ለማሻሻል መሠራቱን ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን የቡሬ መብራት ኀይል ሰብስቴንሽን ግንባታ ችግሮችን በመቅረፍ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።
በዞኑ ሰባት የሚኾኑ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው ስድስት ፕሮጀክቶች ወደ ተሟላ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በሰከላ እና ቋሪት ወረዳዎች በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን በዚህ ዓመት ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሌላው ለበርካታ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የፍኖተሰላም ሆስፒታል ግንባታን ወደ ሥራ ለማስገባት የክልሉ መንግሥት 600 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ጠቁመዋል።
በቀጣይ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን የተሻለ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
የጸጥታ ሁኔታውን ለማረጋጋት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሕዝባዊ ውይይቶችን በማጠናከር ሰላማዊ አማራጮች ላይ ሰፊ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ለሰላም ሁኔታው መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው ትብብሩን አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
