የበጋ መስኖ ልማት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መፍትሔ ነው።

16

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሰባታሚት ቀበሌ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ፣ የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እና ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የግብርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በቀበሌው በበጋ መስኖ የእርሻ ዝግጅት ሲያደርግ ያገኘነው ወጣት እንዳየሁ አደመ በኩታ ገጠም ማሳ በመስኖ ማልማት ከጀመረ ሦስት ዓመት እንኾነው ገልጿል። የበጋ መስኖ ከፍተኛ ምርት እንደሚያስገኝም ተናግሯል።

የውኃ እና የማዳበሪያ አቅርቦት በቂ እንዳልኾነ አርሶ አደሩ ጠቁሟል። የሞተር ፓምፕ እና የነዳጅ እጥረት መኖሩንም ገልጿል።

ሌላኛው የሰባታሚት ቀበሌ ነዋሪ መኬ ውብሸት በበጋ መስኖ ልማት የዘር ድጋፍ እና ከግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ እያገኙ መኾኑን ገልጸዋል።

በክረምት መሬቱ ውኃ ስለሚበዛበት ምርታማነቱ አነስተኛ መኾኑን ገልጸው የበጋ መስኖ ልማቱ ግን በእጥፍ ውጤታማ መኾኑን አንስተዋል።

ወጣት ይቻላል ቢያዝንም የበጋ መስኖ ከክረምቱ የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ ገልጾ በዚህም ከአንድ በሬ ወደ ሦስት በሬ ባለቤትነት ማደጉን ገልጾልናል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በዞኑ 44 ሺህ 800 ሔክታር መሬት በመስኖ እንደሚለማ ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥም 29 ሺህ ሄክታሩ በበጋ ስንዴ እንደሚለማ እና እስካሁንም 6 ሺህ ሄክታር መልማቱን ጠቅሰዋል።

ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማነት በንቅናቄ መድረክ ፈጻሚን በማዘጋጀት፣ ሙያዊ ድጋፍ የማድረግ እና የግብዓት እና ቴክኖሎጂ አቅርቦት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዞኑ የማዳበሪያ እጥረት አለመኖሩን ያነሱት መምሪያ ኀላፊው ለበጋ መስኖ ብቻ እንኳ 29 ሺህ ኩንታል ዳፕ እና 58 ሺህ ኩንታል ዩሪያ በመጋዘን መኖሩንም አንስተዋል። ምርጥ ዘር አርሶ አደሮች በራሳቸው እየገዙ እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል።

በዞኑ 1 ሚሊዮን 130 ሺህ ኩንታል ምርት ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን የታቀደውን የበጋ መስኖ ልማት ለማሳካት የሚያስችል በመስኖ የሚለማ ሰፊ መሬት መኖሩን ጠቁመዋል። የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውኃ በብዛት መኖሩ እና ሠርተው ሕይወታቸውን ለመለወጥ የተነሳሱ አርሶ አደሮች መኖራቸው ለዞኑ ልማት ምቹ ሁኔታዎች ናቸውም ብለዋል።

አርሶ አደሮች በበጋም ማምረት እንደሚቻል ተረድተው ወደ ሥራው መግባታቸውንም አንስተዋል።

ልማትን ለማፋጠን የሰላምን አስፈላጊነት ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው የዞኑ ሰላም እየተሻሻለ መኾኑን ገልጸዋል። ሕዝቡም ሰላም እና ልማት ፈላጊ መኾኑን ጠቅሰዋል። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም የመግንሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም እየመጡ ነው፤ ይህንን ዕድል በመጠቀምም ልማቱን እያፋጠንን ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ የመልማት አቅም እንዳለ ገልጸዋል። እካሁን የለማው 331 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘንድሮ 198 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ይለማል፤ በቀጣይ ወደ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ለማሳደግ ይሠራል ብለዋል። አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም ብለን ለመሥራት ተነስተናል ብለዋል።

መስኖ ከዝናብ ጥገኝነት የሚያወጣ የአመራረት ስልት ነው። የበጋ መስኖ ልማት በየዓመቱ ውጤት እና እድገት የታየበት ነውም ብለዋል። በምግብ ራስን የመቻያ ዋና መንገድ መኾኑንም ነው የገለጹት።

የበጋ መስኖ ልማት በየዓመቱ መሻሻል የሚታይበት ነው ያሉት ኀላፊው ባለፈው ዓመት 208 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቅሰው ዘንድሮ ደግሞ 350 ሺህ ሄክታር እንደሚለማ እና 210 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ከበጋ መስኖ ለማምረት መታቀዱንም ኀላፊው አንስተዋል። እስካሁን 284 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቶ በኩታገጠም የማደራጀት እና የግንዛቤ ፈጠራ ተሠርቷል ነው ያሉት። 181 ሺህ ሄክታር የእርሻ ዝግጅት እና 63 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በስንዴ ዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ለመኸር እርሻ እና ለመስኖ ምርት ለማቅረብ ከታቀደው ውስጥ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱንም ገልጸዋል።

በዩኒየኖች በቂ አቅርቦት መኖሩንም ነው ኀላፊው የተናገሩት። የማዳበሪያ እጥረት አለመኖሩንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሥልጠና ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር መቀየር ከቻላችሁ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleኅብረተሰቡ ለሰላም እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ተጠየቀ።