
አዲስ አበባ: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የማሊዥያ እና የሲንጋፖር መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ትብብር ማደግ ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ ብለዋል።
ከሀገራቱ ጋርም በነዳጅ፣ በታዳሸ ኃይል፣ በሥራ ፈጠራ፣ በሲቪል ሰርቪስ አሥተዳደር፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ እና በዲጂታል ፋይናንስ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በቅርቡ ስሎቫኒያ፣ ኮሎምቢያ፣ ስሎቫኪያ እና ማሊዥያም በአዲስ አበባ አዳዲስ ኤምባሲ ከፍተው ሥራ መጀመራቸውን አስታውሰዋል። ቃል አቀባዩ ሰሞኑን ደግሞ ሲንጋፖር እና ሀይቲ በአዲስ አበባ ኤምባሲያቸውን ለመፍከፈት በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።
ይህም የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እየተጠናከረ መምጣቱን ማሳያ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳውዲ አረቢያ ብቻ ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ17 በረራዎች 22 ሺህ 955 ዜጎችን መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።
ላኦስ፣ ካምቦዲያ እና ማይናማር ላይም በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን የመመለስ ተግባር እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል። ሰሞኑን ከማይናማር ብቻ 300 ሰዎችን ከእገታ ማስለቀቅ የተቻለ ሲኾን 34ቱን ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል ብለዋል።
3ኛው የኢጋድ የሽልማት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ አንደሚከናወንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
