
አዲስ አበባ፦ ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ በከባቢያዊ፣ ማኅበራዊ እና አሥተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ከጀርመን ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነት ላይ ትኩረት በሚያደርጉ ቁልፍ መስኮች ላይ ለመሥራት የሚያስችል መኾኑን የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የኋላ ገሠሠ ገልጸዋል።
ሥምምነቱ ዓባይ ባንክ በፋይናንስ ዘርፉ ከሚሠራቸው ተግባራት በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃ፣ በደንበኞችና ሠራተኞች ደኅንነት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ የሚያስችል መኾኑም ተናግረዋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል “ግሪን ባንኪንግ” የተሰኘ አገልግሎት እንደሚሰጥ የገለጹት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ሥምምነቱ ይህንን የባንኩን አገልግሎት የሚያጠናክር ይኾናልም ብለዋል።
የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት የአፍሪካ ፕሮጀክት አስተባባሪ ኦሊቨር ሻስተር ይህ ስምምነት ዓባይ ባንክ በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሠራቸውን ሥራዎች የሚደግፍ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልሳ ጉኡሽ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
