“የነገዋ ኢትዮጵያ የነገ ተሰፋዋ በዛሬ ወጣቶቿ ትከሻ ላይ ያረፈ ነው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)

22

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ሰፊ የሰብዓዊ ቀውስን ያስከተለው፣ የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ ያቀጨጨው፣ የማኅበረሰቡን እሴት የሸረሸረው እና የሕዝቡን ሥነ ልቦና የጎዳው የእርስ በእርስ ግጭት ከተከሰተ ጥቂት ዓመታትን አስቆጠረ፡፡

ግጭቱን ተከትሎ በተፈጠረ ዙሪያ መለስ ቀውስ ውስጥ ደግሞ ግንባር ቀደም ተጎጂ ኾኖ የቆየው የክልሉ ሕዝብ ነው፡፡

በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጦ ቆይቷል፣ የጤና አገልግሎቶችን አስተጓጉሏል፣ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት የሚገነቡ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተጓትቷል፣ ማኅበራዊ መስተጋብር እክል ገጥሞት ቆይቷል፣ ተቋማት የጥቃት ሰለባ ኾነዋል፣ እንቅስቃሴ ተገትቷል ይህንንም ተከትሎ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ተስፋፍተው ቆይተዋል፡፡

በአጠቃላይ የክልሉ ሕዝብ በተፈጠረው ቀውስ ማኅበራዊ እረፍት ርቆት ቆይቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ለሀገረ መንግሥት አደጋ እስከመኾን ደርሶ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ተቀልብሶ በበርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል፡፡

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎም የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ባደረጉት ተደጋጋሚ ውይይቶች በክልሉ ያደገ ሰላም ተፈጥሯል ያሉን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ናቸው፡፡

መንግሥት ከሰላም አማራጮቹ ጎን ለጎን የክልሉን የጸጥታ መዋቅር መልሶ በማደራጀት እና በማጠናከር ግዳጅን በብቃት የመፈፀም አቅም ፈጥሯል ያሉት ኀላፊው የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን በመተው ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያድርጉ ኀይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ቢቀለበስም አሁንም ሕዝብን የሚረብሹ እና የሌሎችን ተልዕኮ የሚያስፈጽሙ ታጣቂዎች እንዳሉ ግን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ቀጣናዊ ልዕልና የሚመነጨው ከውስጣዊ አንድነቷ ነው ብለው የሚያምኑ ታሪካዊ ጠላቶች አሉ ያሉት ዶክተር እሸቱ የሱፍ እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች የሚጠቀሟቸው ደግሞ የውስጥ ታጣቂዎችን ነው ይላሉ፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለዓላማዎቻቸው መጠቀሚያ ማድረግ የሚፈልጉ ጠላቶች እጆቻቸውን እንዳስገቡም አንስተዋል፡፡

ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ነባራዊ እውነቱን እና ሁኔታዎችን በሰከነ መንግድ መረዳት እና የሰላም አማራጩን መጠቀም ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ኀላፊው ሕዝቡም ከውይይት እና ሰላማዊ ትግል የወጡ የግጭት አማራጮችን ሊቃወም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በግጭት ክልሉን የበለጠ ከማዳከም ባለፈ ለውጥ እንደማይመጣ ግን በተደጋጋሚ ታይቷል ብለዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ያጋጠመውን ሰብዓዊ ኪሳራ የሚቸበችቡ የመገናኛ ብዙኅን መኖራቸውን ያነሱት ዶክተር እሸቱ ማኅበራዊ ኀላፊነትን ለመወጣት እውነትን መሠረት አድርገው ሊሠሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

“የነገዋ ኢትዮጵያ የነገ ተሰፋዋ በዛሬ ወጣቶቿ ትከሻ ላይ ያረፈ ነው” ያሉት ኀላፊው ወጣቶች ከእነዕውቀታቸው፣ ተስፋቸው፣ ኀይላቸው እና አቅማቸው የግጭት ሰለባ መኾን የለባቸውም ነው ያሉት፡፡

ከስሜት ወጥቶ የአዋጊዎችን ፍላጎቶቻቸውን ማጤን እና ምክንያታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕልምን እንደ ፊልም
Next articleዓባይ ባንክ ከጀርመን ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።