ሕልምን እንደ ፊልም

31

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሕልም ምንድን ነው? የሚለውን ሃሳብ ከቀላል የመዝገበ ቃላት ትርጓሜው ተነስተን ምንነቱን ዳስሰን ዛሬ በቴኮኖሎጂ ጉዳይ ለምን እንደመጣ እንቃኛለን።

ሕልም በእንቅልፍ ላይ እያለን የሚከሰት ከቁጥጥር ውጭ የኾነ የምስል እና የስሜት ፍስሰት ነው የሚል ፍቺን በመዝግበ ቃላት ውስጥ ይዞ እናገኘዋለን [ሜሪየም ዌብስተር]።

ሳይንስም ይህን ሃሳብ የሚጋራው ይመስላል። ጤና ነክ መረጃን የሚያጋራ ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ የተሰኘ ድረ ገጽ ሕልም በእንቅልፍ ወቅት በአዕምሯችን የሚፈጠር ምስል እና ታሪክ መኾኑን ገልጾ በቀን ውሏችን አዕምሯችን የሰበሰበውን መረጃ ለማቀናበር የሚረዳ ነው ይላል።

ድረ ገጹ ያወጣው ጽሑፍ ምንም እንኳን ሁሉንም ሕልም ልናስታውስ ባንችልም ሁሌም ስንተኛ ከ3 እስከ 6 ጊዜ ልናልም እንደምንችል እና እያንዳንዱ ሕልም ደግሞ ከ5 እስከ 2ዐ ደቂቃ ርዝማኔ ሊኖረው እንደሚችል ይጠቁማል።

በጣም የሚገርመው ደግሞ 95 በመቶ የሚኾነው ሕልማችን ከዕንቅልፍ ስንነቃ የማናስታውሰው መኾኑን ያትታል።

የሕልሞን ምንነት እንደመንደርደሪያ አነሳን እንጂ የጽሑፋችን መዳረሻ ከወደ ጃፓን የተፈጠረው ሕልምን በምስል ከስቶ የሚያሳይ ቴክኖሎጂ ነው።

በጃፓን የሚገኙ የሥርዓተ ነርቭ ሳይንስ ተመራማሪዎች በደም ፍሰታችን ከሚኖሩ ለውጦች በመነሳት የአንጎላችንን ተግባራት በምስል የሚያሰቀምጥልን መሳሪያ (fMRI) እና የሰው ሠራሽ አስተወሎትን በመጠቀም የሰዎችን ሕልም በምስል መከሰት የሚችል የምርምር ውጤት ማስተዋወቃቸውን ቨርዲክት የተሰኘው የዩኬ ድረ ገጽ አስነብቧል።

በዚህ የምርምር ሥራ ሙከራ ሂደት ውስጥ በርካታ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት ሲኾን ቴክኖሎጂው እነዚህ ተሳታፊዎች በተኙበት ወቅት በሚገጠምላቸው መሳሪያ አማካይነት የአንጎላቸውን የኤሌክትሪክ እና የደም ዝውውር በማጥናት ሊታይ ወደሚችል ተንቀሳቃሽ ምስል ይቀይራል።

ለሙከራው የተሳተፉ ሰዎች ለበርካታ ቀናት በሚተኙበት ወቅት አንጎላቸው ያለው እንቅስቃሴ እየተቀረጸ ይቀመጣል።

የአንጎል እንቅስቃሴ ሲጨምር እና ሕልም መከሰት ሲጀምር ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ ይደረጉ እና ሕልማቸውን ይናገራሉ። ይህ ሂደት ለበርካታ ጊዚያት እየተደጋገመ የሰዎቹ የአንጎል እንቅስቃሴ እና ያዩት ሕልም እየተቆራኘ ወደ መረጃ ቋት ይጠራቀማል።

በዚህ የመረጃ ቋት (database) ላይ የተጠራቀመው መረጃ በጥልቅ አስተውሎት ሥልተ ቀመር (deep learning algorithm) ምስል እንዲከስት ይደረጋል።

በሙከራው ወቅት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚኾን የትክከለኛነት ውጤት መገኘቱም ተጠቅሷል።

ቴክኖሎጂው ሕልምን እንደ ፊልም በምስል ከስቶ ማሳየቱ በራሱ ድንቅ ነገር ቢኾንም በጤናው ዘርፍ ለሥርዓተ ነርቭ እክል ሕክምና የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መኾኑን ድረ ገጹ ጠቁሟል። ለወደፊት ሊታዩ የማይችሉ የአዕምሮ ጤና ችግሮችን ለመመርመር እና ለመረዳት የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚኾንም ተመላክቷል።

ቴክኖሎጂው እየጎለበተ ሲሄድ ስለንቁው (conscious) እና ድብቁ (subconscious) የአዕምሯችን ክፍል ያለንን መረዳት ከፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ተስፋ ተጥሎበታል።

በዘመኑ መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከዐይን ሞራ ቀዶ ሕክምና በኋላ ለዕይታ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ታካሚዎች ገለጹ።
Next article“የነገዋ ኢትዮጵያ የነገ ተሰፋዋ በዛሬ ወጣቶቿ ትከሻ ላይ ያረፈ ነው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)