
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የፀሐይ ግርዶሽ የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን በመገንዘብ ክስተቱን መመዝገብ እንደሚገባ ሊቃውንት መክረዋል፡፡
የፊታችን እሑድ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም በዓለም ሰማይ ላይ ፀሐይ በጨረቃ ትሸፈናለች፤ በከዋክብትም ትከበባለች፤ ሰማይም ልዩ ገጽታ ይኖራታል፡፡ ያልሰሙት ሲደናገጡ የሰሙት ደግሞ ይደነቃሉ፡፡ ቀኑም የተለዬ ይሆናል፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ስለሚኖረው የፀሐይ ግርዶሽ ከአብመድ ጋር ቆይታ የነበራቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሐዲሳት መምህርና የጥንታዊ ጽሑፍ ታሪክ ተመራማሪ መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) እና የአስትሮ ፊዚክስ ምሁሩ ዶክተር ጌትነት ፈለቀ ቀኑን አስመልክተው የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ዕወቅት እና የዘመኑን ሳይንስ እያጣቀሱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የጠፈር ምርምር ሰማያዊ አካላትን የሚመረምር ሳይንስ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ዘርፍ ቀዳሚ ከነበሩ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ጥንታዊ የጠፈር ምርምር ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገራት ብቸኛዋ ያደርጋታል፡፡ የሥነ ፈለክን ወይም የሥነ ከዋክብትን ጥናት የጀመሩ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ስለፕላኔቶችም ስያሜ የሰጡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከዛሬ አራት ሺህ ዓመት በፊት ከንግሥት ካስዮፕያ እስከ ባለቤቷ ሴፈስ፣ ከልጃቸው ልዕልት አንድሮሜዳ እስከኋለኞቹ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በሰማይ ስላሉ አካላት በብራናቸው በማይጠፋ ቀለማቸው ከትበው አልፈዋል፤ በስማቸውም ሰይመዋቸዋል፡፡
ቆይቶ የተነሳው ግሪካዊው አስትሮኖመር ፕቶሎሚም 48 ኅብረ ከዋከብትን ሲመዘግብ ሦስቱን ለኢትዮጵያ ሰጥቶ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ኅብረት በ1930ዎቹ ሲመዘግብ በመጀመሪያ የመዘገበው የልዕልት አንድሮሜዳዋን ስያሜ ኮከብ ነበር፡፡ ጠቢቡ ንጉሥ ላልይበላ ከአንድ አለት ላይ 11 አብያተ ክርስቲያናትን ስለሠራ በዚህ ብቻ ስሙ ከፍ ቢልም የሒሳብና የሥነ ፈለክ ቀመርም ፈጥሯል፡፡ ንጉሡ ከማንም በመቅድም የራሱ የሆነ የሰማይ ምልከታ ቦታ እና መመልከቻ መሳሪያም ነበረው፡፡
በሕዋ ሳይንስ ከሚታወቀው የማይታወቀው እንደሚበልጥ ዶክተር ጌትነት ተናግረዋል፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ስለግርዶሽ በሚገባ ጽፈው እንዳስቀመጡ ደግሞ መጋቢ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አስደናቂና አስፈሪ የነበሩ ግርዶሾች ስለመመዝገባቸው ታሪኩን እያጣቀሱ ሊቃውንቱ አስረድተዋል፡፡ በ1545 ዓ.ም ከአጽናፍ ሰገድ አጼ ገላውዴዎስ እስከ አዕላፍ ሰገድ ጻዲቁ ዮሐንስ ኅዳር 5 ቀን 1661 ዓ.ም፣ ከጻዲቁ ንጉስ ዮሐንስ መጋቢት 24 ቀን 1672 ዓ.ም እስከ ዳግመዊ እስክንድር አጼ በካፋ 1720 ዓ.ም የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በተለይም በአፄ ባካፋ ዘመነ መንግሥት የነበረውን ግርዶሽ መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታሪከ ነገሥትን ዋቢ አድርገው ሲያስረዱ “ዳግማዊ እስክንድር አጼ በካፋ በነገሠ በ6ኛው ዓመት በወርኃ መስከርም በሰባተኛው ቀን ሦስት ሰዓት ላይ ፀሐይ ጨለመች፡፡ ከዋክብትም ታዩ፣ ሰው ሁሉ ታወከ፣ ለመኑም፣ ፀሐይም እንደገና በራች” በማለት ግርዶሹ ሲከሰት ሰው እንዴት ተደናግጦ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ግርዶሽ ብቻ ሳይሆን ጅራታማ ኮኮብ ሲታይም ከትበው አስቀምጠው ነበር፤ የዘንድሮው ግርዶሽ ለዬት ያለ ግርዶሽ ስለመሆኑም ሊቃውንቱ አብራርተዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝንና የግርዶሹን መገጣጠም በተመለከተ ደግሞ ‘‘ፀሐይ ሦስት ክፍሎች አሏት፤ የሚታዬው ብርሃናማው ክፍል ‘ፎቶስፌር’ ይባላል፣ ከሱ ቀጥሎ ያለው ውጫዊ ከባቢ አየር ‘ክሮሞስፌር’ ይባላል፤ የፀሐይ የመጨረሻው ክፍልና አክሊል መስሎ የሚታዬው ከባቢ አየር በሳይንሱ ‘ኮሮና’ ይባላል፡፡
ግርዶሹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስድስት ሰዓታት እንደሚቆይም ተነግሯል፡፡ ከቶጎ በመነሳትፓስፊክ ውቂያኖስ ላይ እንደሚያበቃም የምሁራኑ ትንታኔ ያመላክታል፡፡ ጠዋት 12፡45 ጀምሮ ቀን 6፡33 ላይ እንደሚያበቃም ተገምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከረፋዱ 3፡19 ላይ ግርዶሹ ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይም ለ2 ደቂቃ ከ35 ሰኮንዶች እንደሚቆይ ነው የተጠበቀው፡፡
ግርዶሽን መመልከቻ የሚመከሩ መነጸሮች አሉ፡፡ ሰዎች በተለያዩ መሳሪያዎች ግርዶሹን ለማዬት መዘጋጀታቸው ትክክል አለመሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ሰዎች መዘናጋትና ለጉዳት መጋለጥ እንደማይገባቸውም መክረዋል፡፡
ይህን ውብ ተፈጥሮ በመደናገጥ ሳይሆን በመደነቅ ማሳለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን የተፈጥሮ ክስተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ክስተቱን በመመዝገብ ታሪኩን ማስቀረት እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡
የኮሮና ቫይረስ ባይከሰት ኖሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተመራማሪዎች በዚህ ቀን ኢትዮጵያን ለማዬት እቅድ ይዘው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘርፍ የረቀቁ ነበሩ ያሉት ምሁራኑ ነገር ግን ዘመናዊ በተባለለት በዚህ ትውልድ ዘንድ ሥነ ፈለክን የማያውቀው ብዙ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
