ከዐይን ሞራ ቀዶ ሕክምና በኋላ ለዕይታ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ታካሚዎች ገለጹ።

18
በደብረብርሃን: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኪውር ብላይንድነስ ጋር በመተባበር የዐይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና እየሰጠ ነው።
የሆስፒታሉ ሥራ አሥኪያጅ ጥላሁን ሙሉጌታ ሕክምናው ባለፉት ዓመታት ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰው አሁንም ከ2ሺህ በላይ ታካሚዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ ብለዋል።
የሕክምና ወጭዎችንም ኪውር ብላይንድነስ የተሰኘው የአሜሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት እደሚሸፍን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ የዐይን ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዓለማየሁ ባዩ የዐይን ሞራ ግርዶሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰተው የዐይነ ስውርነት ችግር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሕክምናው ውጤታማ ከሚባሉ የቀዶ ሕክምና አይነቶች አንዱ በመኾኑ የሕክምና አገልግሎቱን እንዳገኙ የዐይን ብርሃናቸው እንደሚመለስም አስረድተዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ሕክምናው በሆስፒታሉ መሰጠቱ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
ለሕክምናው ከአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ የመጡት ታካሚ መሐመድ ይመር “ባለቤቴን እና ግመሎቼን ካየኋቸው ሁለት ዓመት አልፎኝ ነበር፣ አሁን ግን በሕክምናው ባለቤቴን በዐይኔ በማየቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።
ከሸዋሮቢት ከተማ ለሕክምና መጥተው አሚኮ ያገኛቸው ሌላኛዋ ታካሚ አሚናት አወል ለሁለት ዓመት የሚበሉትን እና የሚለብሱትን እንኳን ባለማየታቸው ሲያዝኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ሕክምና ተደርጎላቸውም የዐይን ብርሃናቸው በመመለሱ ደስታቸው ከቃል በላይ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
የዐይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምናው እስከ ኅዳር 20/2018 ዓ.ም እንደሚሰጥም ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፦ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበተባበሩት መንግሥታት የአየርንብረት ለውጥ ማሕቀፍ ኮንቬንሽን መሠረት የኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሀገር መሆኗን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን የኮፕ 32 ተወካይ ፕሬዝደንት አድርጎ መመደቡን ሲገልጽ ደስታ ይሰማዋል።
Next articleሕልምን እንደ ፊልም