
ባሕር ዳር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው የዓለም ኤድስ ቀን “ተግዳሮቶችን በመቋቋም ኤች አይቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም ለ38ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ የአማራ ክልል ጤና ቢሮም አከባበሩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመው በዓሉ ሲከበር የተዘነጋ የሚመስለውን እና ሥርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ ተግባራት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመግለጫው እንደተገለጸው በክልሉ በዓመት ውስጥ 3 ሺህ 414 ሰዎች በአዲስ በኤች አይ ቪ ይያዛሉ፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኤች አይ ቪ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት
ጦርነት፣ የትምህርት ቤቶች መቋረጥ፣ ስለ ኤች አይ ቪ ያለው የተሟላ ግንዛቤ ዝቅተኛ መኾን፣ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ መፈጸም እና ሌሎችም ተጠቅሰዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከልም ይበልጥ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የባሕሪ ለውጥ እንዲያመጡ ማስተማር እና ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
የአመራሩ እና የሕዝብ አጀንዳ እንዲኾን ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮች፣ የሙያ ማኅበራት እና የማኅበረሰብ ተቋማት አመራሮች ሚና የጎላ መኾን ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡
የዓለም ኤድስ ቀን ሲከበር መላው ሕዝብ በንቅናቄ እንዲያከብረው እና ለቫይረሱ ሥርጭት መዘናጋቱን እንዲያቆም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
